2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2:14-26

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2:14-26 መቅካእኤ

ይህን አሳስብ፤ እንዲሁም በቃላት እንዳይከራከሩ በእግዚአብሔር ፊት እዘዝ፤ ይህ የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ምንም ጥቅም የለውምና። የእውነትን ቃል በትክክለኛው መንገድ እየገለጥህ፥ የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ፥ ለእግዚአብሔር ብቁ ተደርገህ ራስህን ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጣር። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ምክንያቱም ሰዎችን ከፊት ይልቅ ወደ ኃጢአት ይመራልና፤ ቃላቸውም እንደ ቈላ ቊስል ይባላል፤ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ከእነርሱ መካከል ናቸው፤ እነዚህም፦ “ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል፤” እያሉ በእውነት ነገር ስተው ሄደዋል፤ የአንዳንዶችንም እምነት አጥፍተዋል። ሆኖም የእግዚአብሔር ጠንካራ መሠረት የቆመው፦ “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዐመፅ ይራቅ፤” የሚለውን ማኅተም ታትሞ ነው። በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ የእንጨትና የሸክላ ዕቃዎችም ደግሞ ይኖራሉ፤ እኩሌቶቹም ለክብር፥ እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ለውርደት ከሚሆነው ነገር ራሱን ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን፥ የተቀደሰ፥ ለጌታውም የሚጠቅም፥ ለመልካምም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ጠብንም እንደሚያመጡ ታውቃለህና ከሞኝነትና ከከንቱ ንትርክ ራቅ። የጌታም ባርያ ጠበኛ መሆን አይገባውም፤ ይልቁንስ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ ትዕግሥተኛና የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚገሥጽ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህም የተነሣ ምናልባት እግዚአብሔር ንስሓ ገብተው እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፥ እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም ታስረው ከተያዙበት ከዲያብሎስ ወጥመድ ወጥተው ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋልና።