ይህን ነገር አስገንዝባቸው፤ በቃላት ምክንያት እንዳይከራከሩም በጌታ ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ የቃላት ክርክር የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ለምንም አይጠቅምም። የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያደርስና በሥራውም እንደማያፍር ሠራተኛ ሆነህ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብና ተቀባይነትን ለማግኘት ጥረት አድርግ። ዓለማዊና ከንቱ ከሆነ ልፍለፋ ራቅ፤ እንዲህ ዐይነቱ ልፍለፋ ሰዎችን ይበልጥ ከእግዚአብሔር እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፤ የእነርሱ ንግግር እንደማይድን ቊስል ይቦረብራል፤ ከእነርሱም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች “የሙታን ትንሣኤ ገና ዱሮ ሆኖአል” እያሉ በመከራከር ከእውነት ርቀዋል፤ የአንዳንዶችንም ሰዎች እምነት ያናውጣሉ። ነገር ግን “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይኖራል። በትልቅ ቤት ውስጥ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ ከእንጨትና ከሸክላ የተሠሩ ዕቃዎችም ይገኛሉ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ለተከበረ አገልግሎት፥ አንዳንዶቹም ክብር ለሌለው አገልግሎት ይውላሉ። ከእነዚህ ክብር ከሌላቸው ነገሮች ተለይቶ ንጹሕ ሆኖ የሚኖር ሰው ለተከበረ አገልግሎት እንደሚውል ዕቃ ይሆናል፤ ለማንኛውም መልካም አገልግሎት የተዘጋጀ ለጌታው የተቀደሰና ጠቃሚ መገልገያ ይሆናል። ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ሰዎች ጋር ሆነህ ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን ተከታተል። ጠብን እንደሚያመጣ ዐውቀህ ከሞኝነትና ከከንቱ ክርክር ራቅ። የጌታ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነ ሰው በሁሉም ዘንድ ገር፥ የማስተማር ችሎታ ያለውና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት እንጂ መጣላት አይገባውም፤ እርሱ የሚቃወሙትን ሰዎች በገርነት የሚያርም መሆን አለበት፤ ምናልባትም እውነትን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ንስሓ የመግባትን ዕድል ይሰጣቸው ይሆናል። በዚህ ዐይነት ወደ ልቡናቸው ተመልሰው ዲያብሎስ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ እነርሱን ከያዘበት ወጥመድ ያመልጣሉ።
2 ወደ ጢሞቴዎስ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ወደ ጢሞቴዎስ 2:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች