ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም፦ ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ። ሆኖም፦ ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም፦ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል። በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።
2 ወደ ጢሞቴዎስ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ወደ ጢሞቴዎስ 2:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች