2 ጢሞቴዎስ 2:14-26
2 ጢሞቴዎስ 2:14-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህን አሳስባቸው፤ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፤ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኀጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፤ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም “ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል፤” እያሉ ስለ እውነት ስተው የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ። ሆኖም “ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፤” ደግሞም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዐመፅ ይራቅ፤” የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል። በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፤ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማርም የሚበቃ፥ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም “ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሓን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው ወደ አእምሮ ይመለሳሉ፤” ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።
2 ጢሞቴዎስ 2:14-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለ እነዚህ ነገሮች ማሳሰብህን አትተው፤ በቃላት እንዳይነታረኩ በእግዚአብሔር ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ ጥቅም የሌለው፣ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። እንደማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሰከረለት ሠራተኛ፣ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ልታቀርብ ትጋ። እግዚአብሔርን ከማያስከብር ከንቱ ልፍለፋ ራቅ፤ በዚህ ነገር የተጠመዱ ሰዎች ከእግዚአብሔር እየራቁ ይሄዳሉና። ትምህርታቸው እንደማይሽር ቍስል ይሠራጫል፤ ከእነዚህም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ፤ እነዚህም ከእውነት ርቀው የሚባዝኑ ናቸው። እነርሱም ትንሣኤ ሙታን ከዚህ በፊት ሆኗል እያሉ የአንዳንዶቹን እምነት ይገለብጣሉ። ይሁን እንጂ፣ “ጌታ የርሱ የሆኑትን ያውቃል” ደግሞም፣ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሟል። በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን፣ የዕንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ለከበረ፣ ሌሎቹም ለተራ አገልግሎት ይውላሉ። እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ከጠቀስኋቸው ነገሮች ቢያነጻ፣ ለክቡር አገልግሎት የሚውል፣ የተቀደሰ፣ ለጌታው የሚጠቅም፣ ለመልካም ሥራም ሁሉ የተሰናዳ ዕቃ ይሆናል። ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋራም ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ተከታተል። ከማይረባና ትርጕም የለሽ ከሆነ ክርክር ራቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ጠብን እንደሚያስከትሉ ታውቃለህ። የጌታም ባሪያ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቃት ያለው፣ ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል፤ እውነትን ወደ ማወቅ ይደርሱ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን እንደሚሰጣቸው ተስፋ በማድረግ የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚያቃና መሆን ይኖርበታል፤ ይኸውም ወደ አእምሯቸው ይመለሳሉ፤ ፈቃዱን ሊያስፈጽማቸው ምርኮኛ አድርጎ ከያዛቸው ከዲያብሎስ ወጥመድም ያመልጣሉ በማለት ነው።
2 ጢሞቴዎስ 2:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም፦ ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ። ሆኖም፦ ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም፦ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል። በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።
2 ጢሞቴዎስ 2:14-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህን ነገር አስገንዝባቸው፤ በቃላት ምክንያት እንዳይከራከሩም በጌታ ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ የቃላት ክርክር የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ለምንም አይጠቅምም። የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያደርስና በሥራውም እንደማያፍር ሠራተኛ ሆነህ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብና ተቀባይነትን ለማግኘት ጥረት አድርግ። ዓለማዊና ከንቱ ከሆነ ልፍለፋ ራቅ፤ እንዲህ ዐይነቱ ልፍለፋ ሰዎችን ይበልጥ ከእግዚአብሔር እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፤ የእነርሱ ንግግር እንደማይድን ቊስል ይቦረብራል፤ ከእነርሱም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች “የሙታን ትንሣኤ ገና ዱሮ ሆኖአል” እያሉ በመከራከር ከእውነት ርቀዋል፤ የአንዳንዶችንም ሰዎች እምነት ያናውጣሉ። ነገር ግን “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይኖራል። በትልቅ ቤት ውስጥ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ ከእንጨትና ከሸክላ የተሠሩ ዕቃዎችም ይገኛሉ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ለተከበረ አገልግሎት፥ አንዳንዶቹም ክብር ለሌለው አገልግሎት ይውላሉ። ከእነዚህ ክብር ከሌላቸው ነገሮች ተለይቶ ንጹሕ ሆኖ የሚኖር ሰው ለተከበረ አገልግሎት እንደሚውል ዕቃ ይሆናል፤ ለማንኛውም መልካም አገልግሎት የተዘጋጀ ለጌታው የተቀደሰና ጠቃሚ መገልገያ ይሆናል። ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ሰዎች ጋር ሆነህ ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን ተከታተል። ጠብን እንደሚያመጣ ዐውቀህ ከሞኝነትና ከከንቱ ክርክር ራቅ። የጌታ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነ ሰው በሁሉም ዘንድ ገር፥ የማስተማር ችሎታ ያለውና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት እንጂ መጣላት አይገባውም፤ እርሱ የሚቃወሙትን ሰዎች በገርነት የሚያርም መሆን አለበት፤ ምናልባትም እውነትን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ንስሓ የመግባትን ዕድል ይሰጣቸው ይሆናል። በዚህ ዐይነት ወደ ልቡናቸው ተመልሰው ዲያብሎስ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ እነርሱን ከያዘበት ወጥመድ ያመልጣሉ።
2 ጢሞቴዎስ 2:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህን አሳስብ፤ እንዲሁም በቃላት እንዳይከራከሩ በእግዚአብሔር ፊት እዘዝ፤ ይህ የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ምንም ጥቅም የለውምና። የእውነትን ቃል በትክክለኛው መንገድ እየገለጥህ፥ የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ፥ ለእግዚአብሔር ብቁ ተደርገህ ራስህን ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጣር። ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ምክንያቱም ሰዎችን ከፊት ይልቅ ወደ ኃጢአት ይመራልና፤ ቃላቸውም እንደ ቈላ ቊስል ይባላል፤ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ከእነርሱ መካከል ናቸው፤ እነዚህም፦ “ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል፤” እያሉ በእውነት ነገር ስተው ሄደዋል፤ የአንዳንዶችንም እምነት አጥፍተዋል። ሆኖም የእግዚአብሔር ጠንካራ መሠረት የቆመው፦ “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዐመፅ ይራቅ፤” የሚለውን ማኅተም ታትሞ ነው። በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ የእንጨትና የሸክላ ዕቃዎችም ደግሞ ይኖራሉ፤ እኩሌቶቹም ለክብር፥ እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ለውርደት ከሚሆነው ነገር ራሱን ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን፥ የተቀደሰ፥ ለጌታውም የሚጠቅም፥ ለመልካምም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ጠብንም እንደሚያመጡ ታውቃለህና ከሞኝነትና ከከንቱ ንትርክ ራቅ። የጌታም ባርያ ጠበኛ መሆን አይገባውም፤ ይልቁንስ ለሰው ሁሉ ገር፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ ትዕግሥተኛና የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚገሥጽ ሊሆን ይገባዋል። ከዚህም የተነሣ ምናልባት እግዚአብሔር ንስሓ ገብተው እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፥ እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም ታስረው ከተያዙበት ከዲያብሎስ ወጥመድ ወጥተው ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋልና።