ጌታ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።” ከዚያም ዳዊት ለናታን፥ “ጌታን በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፥ “ጌታ ኃጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፥ የጌታ ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፥ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፥ የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን ጌታ ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ወደ ክፍሉ ገብቶም ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። የቤተሰቡ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያሰነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ አብሮአቸውም አንዳች ምግብ አልበላም። በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፥ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ። ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፥ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፥ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፥ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ጌታ ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ። አገልጋዮቹም፥ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፥ ‘ጌታ ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፥ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፥ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ። ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። ጌታም ወደደው፤ ጌታ ሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ። በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ራባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ። ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ራባን ወግቼ የውሃውንም ከተማ ይዤአለሁ፤ እንግዲህ የቀረውን ሠራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ ያለበለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።” ስለዚህ ዳዊት መላውን ሠራዊት አሰባስቦ ወደ ራባ በመሄድ ወግቶ ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት የሚመዝነው አንድ መክሊት ወርቅ ሲሆን፥ በከበረ ዕንቁም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፥ የብረት መቆፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሠራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:11-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች