2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26

26
ዖዝያን መንገሡ
1የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ዕድሜ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። 2ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፥ ወደ ይሁዳም መለሳት። 3ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 4አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 5ጌታንም መፍራት ባስተማረው ዘካርያስ በእርሱም ዘመን ጌታን ለመፈለግ ልቡን አቀና፤ ጌታንም በፈለገ ጊዜ ጌታ ነገሩን አከናወነለት።
6ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ የጌትንና የየብናን የአዞጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም አገር ከተሞችን ሠራ። 7እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን በምዑናውያንም ላይ ረዳው። 8አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ተሰማ። 9ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው። 10ብዙም እንስሶች ነበሩትና በምድረ በዳውና በቈላው በደጋውም ግንብ ሠራ፥ ብዙ ጉድጓድም ማሰ፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና አትክልተኞች ነበሩት። 11ደግሞም ለዖዝያን በሠራዊቱ ውስጥ ለውግያ ብቁ የሆኑ ወታደሮች ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ በአለቃው በመዕሤያና በጸሐፊው በይዒኤል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቁጥራቸው ይወጡ ነበር። 12የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የጽኑዓን ኃያላኑ ቍጥር ሁሉ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። 13ንጉሡንም በጠላቱ ላይ እንዲያግዝ፥ በታላቅ ኃይል ወደ ጦርነት የሚወጣ፥ በትእዛዛቸው ሥር የነበረ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ። 14ዖዝያንም ለሠራዊቱ ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቁርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው። 15በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚቀመጡትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች ሠራ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ አገር ድረስ ተሰማ።
ትዕቢትና ከዳተኝነት
16ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም ጌታን በደለ፤ ወደ ጌታ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ። 17ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማኒያ የጌታ ካህናት ተከትለውት ገቡ። 18#ዘፀ. 30፥7፤8፤ ዘኍ. 3፥10።ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ እንዲህ አሉት፦ “ዖዝያን ሆይ! ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለጌታ እንድታጥን ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከጌታ ዘንድ ክብር አያስገኝልህም።” 19ዖዝያንም ተቈጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በጌታ ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። 20ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም እንዲወጣ አስገደዱት፥ እርሱም ደግሞ ጌታ ቀሥፎት ነበርና ለመውጣት ቸኮለ። 21ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከጌታ ቤት ተነጥሎአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር። 22የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል። 23#ኢሳ. 6፥1።ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ እነርሱም፦ “ለምጻም ነው” ብለው ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ