2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 25

25
አሜስያስ መንገሡ
1አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2ፍጹምም ልብ ሳይኖረው አሜስያስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3መንግሥትም በጸናለት ጊዜ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባርያዎች ገደለ። 4#ዘዳ. 24፥16።አሜስያስ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም ነበር ምክንያቱም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ፥ ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበርና፦ “ሰው ሁሉ በገዛ ኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች ፋንታ አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች ፋንታ አይሙቱ።”
ኤዶማውያን መደምሰሳቸው
5አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፥ በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ሥር እንዲሆኑ አደረገ፤ ዕድሜአቸው ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቈጠረ፥ ለጦርነትም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። 6ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎችን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። 7አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ! ጌታ ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ጋር አይደለምና የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር አይውጣ። 8ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የመርዳትና የመጣል ኃይል ከጌታ ዘንድ ነውና ጌታ በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።” 9አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሠራዊት የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሆን?” የጌታም ሰው እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ “ጌታ ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል።” 10አሜስያስም ከኤፍሬም የመጡትን ሠራዊት ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቁጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፥ ወደ አገራቸውም በጽኑ ቁጣ ተመለሱ። 11አሜስያስም በረታ፥ ሕዝቡንም አውጥቶ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፥ ከሴይርም ልጆች ዐሥር ሺህ ገደለ። 12የይሁዳም ልጆች ደግሞ ዐሥር ሺህ ሰዎችን በሕይወታቸው ማረኩ፥ ወደ ዓለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ እነርሱንም ከዓለቱ ራስ ላይ ጣሉአቸው፥ ሁሉም ተፈጠፈጡ። 13አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮች ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሖሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ሰዎች ገደሉ፥ ብዙ ምርኮም ማረኩ። 14አሜስያስም የኤዶማውያንን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፥ የእርሱም አማልክት እንዲሆኑ አቆማቸው፥ ይሰግድላቸውም ያጥንላቸውም ነበር። 15ስለዚህም የጌታ ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ እንዲህ ብሎ የሚናገረውን ነቢይም ላከበት፦ “ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ለምን ፈለግሃቸው?” 16እርሱም እየተናረ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “በውኑ አንተ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሾመነሃልን? ተው፤ እንዲገድሉህ ለምን ትሻለህ?” ነቢዩም፦ “ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና ጌታ ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ” ብሎ ተወ።
እስራኤል ይሁዳን ድል መንሣቱ
17የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ተማክሮ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ።” 18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮስያስ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ “የሊባኖስ ኩርንችት፦ ‘ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው’ ብሎ ወድ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኩርንችቱን ረገጠ። 19አንተም፦ ‘እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ’ ብለህ ኰርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር አብረህ ለመውደቅ ለምን መከራ ትሻላህ?”
20የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው የጌታ ፈቃድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። 21የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት-ሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 22ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፥ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 23የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤት-ሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 24ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በጌታም ቤት ከዖቤድኤዶም ጋር የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ የንጉሡም ቤት መዛግብት፥ በመያዣ የተያዙትንም ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
አሜስያስ መሞቱ
25የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26የቀረውም የፊተኛውና የኋላኛው የአሜስያስ ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27አሜስያስም ጌታን ከመከተል ከራቀ በኋላ በኢየሩሳሌም ሤራን አሤሩበት፥ ወደ ለኪሶም ኰበለለ፤ ከኋላውም የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩበት፥ በዚያም ገደሉት። 28በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ