2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 18
18
ነቢዩ ሚክያስ ውድቀትን መተንበዩ
1ለኢዮሣፍጥም ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ እርሱም ከአክዓብ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ትስስርን አደረገ። 2ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ እንዲሄድ አባበለው። 3የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፦ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በጦርነቱም ላይ ከአንተ ጋር እንሆናለን” ብሎ መለሰለት።
4ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፦ “የጌታን ቃል አስቀድመህ እንድትጠይቅ እለምንሃለሁ” አለው። 5የእስራኤልም ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን ሰብስቦ፦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። 6ኢዮሣፍጥ ግን፦ “እንድንጠይቀው የጌታ ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። 7የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ጌታን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ስለ እኔ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው።” ኢዮሣፍጥም፦ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው። 8የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፦ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። 9የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢትን ይናገሩ ነበር። 10የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ። 11ነቢያትም ሁሉ፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድ፥ ለአንተም ይከናወንልሃል” እያሉ ተመሳሳይ የሆነን ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልክተኛ ሚክያስን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ ድምፅ ሆነው ለንጉሡ መልካም ነገር ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ።” 13ሚክያስም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። 14ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፦ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። እርሱም መለልሶ እንዲህ አለው፦ “ውጣ፥ ይከናወንልህ፤ በእጅህም ተላልፈው ይሰጣሉ።” 15ንጉሡም፦ “በጌታ ስም ከእውነት በቀር ምንም ዓይነት ነገር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 16#ዘኍ. 27፥17፤ ሕዝ. 34፥5፤ ማቴ. 9፥36፤ ማር. 6፥34።ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ” 17የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው። 18ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 19ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ እንዲወድቅ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ያታለለው ማን ነው?’ አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። 20መንፈስም መጣ፥ በጌታም ፊት ቆሞ፦ ‘እኔ አታልልዋለሁ’ አለ። ጌታም፦ ‘በምን ዓይነት መንገድ?’ አለው። 21እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ።’ ጌታም እንዲህ አለው፦ ‘ታታልለዋለህ፤ ይከናወንልሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ። 22እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ ጌታ በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አኑሮአል፤ ጌታም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።’”
23የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና እንዲህ አለ፦ “የጌታ መንፈስ ከአንተ ጋር ለመነጋገር በምን ዓይነት መንገድ ከእኔ አለፈ?” 24ሚክያስም፦ “እነሆ፥ በዚያን ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ይታይሃል” አለው። 25የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ 26እናንተም እንዲህ በሉ፦ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በወህኒ ቤት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት።’ ” 27ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “በደህና የተመለስህ እንደሆነ ጌታ በእኔ አልተናረም።” ዳግመኛም እርሱ፦ “እናንተ ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙኝ!” አለ።
ንጉሥ አክዓብ መሸነፉና መሞቱ
28የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። 29የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፦ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ጦርነቱም ገቡ። 30የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበር፦ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ።” 31የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፦ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፥ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ ጌታም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። 32የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 33አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም፦ “ተወግቻለሁና ሠረገላውን አዙር ከጦርነቱም ውስጥ አውጣኝ” አለው። 34በዚያም ቀን ጦርነቱ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሠረገላው ላይ ራሱን አስደግፎ ተንጋለለ፤ ፀሐይም በጠለቀች ጊዜ ሞተ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 18: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ