2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 17
17
ኢዮሣፍጥ መንገሡ
1በእርሱ ፋንታ ልጁ ኢዮሣፍጥ በየይሁዳ ላይ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ኃይሉን አጠናከረ። 2በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፥ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ። 3በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና ጌታም ከኢዮሣፍጥ ጋር ነበረ፤ በኣሊምንም አልፈለገም፥ 4ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ እንደ እስራኤልም ያለ ሥራ አልሠራም። 5ስለዚህም ጌታ መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሣፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ሀብትና ክብር ሆነለት። 6ልቡም በጌታ መንገድ ላይ ለመመላለስ ድፍረት ነበረው፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ።
7በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች እንዲያስተምሩ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ላከ። 8ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያን ላከ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን አብሮ ላከ። 9እነርሱም የጌታን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር።
10በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ጌታ ፍርሃት አሳረባቸው፥ ከኢዮሣፍጥም ጋር አልተዋጉም። 11ከፍልስጥኤማውያንም ለኢዮሣፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበሩ፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር። 12ኢዮሣፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሠራ። 13በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩት። 14ቁጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ 15ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 16ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለጌታ የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። 17ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 18ከእርሱም በኋላ ዩዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለጦርነት የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ። 19ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 17: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ