2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16
16
ሶርያ ቃል ኪዳን ማድረጓ መወገዙ
1አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። 2አሳም ከጌታ ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ወደ ተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር እንዲህ ብሎ ላከ፦ 3“በአባቴና በአባትህ መካከል እንደነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሁን፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ።” 4ወልደ አዴር ንጉሡን አሳን እሺ አለው፥ የሠራዊቱንም የጦር አዛዦች በእስራኤል ከተሞች ላይ ላከ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና ለንፍታሌም እንደ ግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ያዙ። 5ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፥ ሥራውንም አቋረጠ። 6ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
7በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ ዓናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በጌታ አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል። 8ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ሠራዊት አልነበሩምን? በጌታ ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥ 9ጌታ ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ለማጽናት ዐይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። እንግዲህ አሁን የሞኞችን ተግባር ፈጽመሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ጦርነት ይደረግብሃል።” 10አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በቊራኛ አስሮ በወህኒ ቤት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ፥ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አሠቃየ።
አሳ በደዌ ተጠቅቶ መሞቱ
11የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 12በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ ጌታን አልፈለገም። 13አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። 14ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቶ በተሞላው አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ