2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 15
15
1የጌታም መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ መጣ፤ 2አሳንም ሊያገኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ “አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤ እናንተ ከጌታ ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉትም ታገኙታላችሁ፤ ብትተውት ግን ይተዋችኋል። 3እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። 4በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። 5በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ሁከት ስለ ነበር በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረውም። 6ጌታ በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር። 7እናንተ ግን ለሥራችሁ ሽልማት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ።”
8አሳም እነዚህን ቃላትና የነቢዩን የዖዴድን#15፥8 የዖዴድ ልጅ የአዛርያን። ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በጌታም ቤት ፊት የነበረውን የጌታን መሠዊያ አደሰ። 9ጌታ አምላኩም ከእርሱ ጋር እንደሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ። 10አሳም በነገሠ ዐሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለጌታ ሠዉ። 12በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ለመሻት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ 13የእስራኤልንም አምላክ ጌታን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ እንዲገደል ማሉ። 14ለጌታም በታላቅ ድምፅና በዕልልታ፥ እምቢልታንና ቀንደ መለከትንም እየነፉ ማሉ። 15በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥ በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ ጌታም በዙሪያቸው እረፍት ሰጣቸው።
16ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት#15፥16 አሼራ። ስላደረገች ከእቴጌነትዋ ሻራት፤ አሳም ምስልዋን ቈርጦ ቀጠቀጠው፥ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው። 17በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ። 18አባቱም የቀደሰውን፥ እርሱም ራሱ የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ ጌታ ቤት አገባ። 19አሳም እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ጦርነት አልነበረም።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ