2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19

19
1የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ። 2ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ ጌታን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከጌታ ዘንድ ቁጣ ሆኖብሃል። 3ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድሪቱ አስወግደሃልና፥ ጌታን ለመፈለግ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል።”
ኢዮሣፍጥ ማሻሻያ ማድረጉ
4ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ዳግመኛም ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ ጌታ መለሳቸው። 5በምድሪቱም ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ። 6ፈራጆቹንም እንዲህ አላቸው፦ “ለጌታ እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ልብ ብላችሁ ተገንዘቡ። 7እንግዲህ አሁን ጌታን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በጌታ ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉንም ነገር ተጠንቅቃችሁ አድርጉ።”
8ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በጌታ ስም ፍርድን እንዲፈርዱ በሙግትም ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 9እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “እንዲህ ስታደርጉ ጌታን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። 10በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻቸሁ ዘንድ ስለ ደም መፋሰስ ስለ ሕግና ስለ ትእዛዝ ስለ ሥርዓትና ስለ ፍርድም ማናቸውም ጉዳይ ወደ እናንተ ቢመጣ ጌታን እንዳይበድሉ፥ ቁጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11እነሆም፥ ለጌታ በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሹመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ ጌታም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ