2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20
20
ከምሥራቅ በኩል የመጣ ወረራ
1እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ። 2ሰዎችም መጥተው እንዲህ በማለት ለኢዮሣፍጥ አወሩለት፦ “ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዐይን-ጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ይገኛሉ።” 3ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ ጌታንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ። 4ይሁዳም ጌታን ይፈልግ ዘንድ ተሰበሰበ፤ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ጌታን ለመሻት መጡ።
የኢዮሣፍጥ ጸሎትና ማሸነፍ
5ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በጌታ ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤ 6እርሱም እንዲህ አለ፦ “አቤቱ፥ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ! በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም። 7#ኢሳ. 41፥8፤ ያዕ. 2፥23።አምላካችን ሆይ! በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘለዓለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን? 8እነርሱም ተቀመጡባት፥ ለስምህም መቅደስን ሠርተውባት እንዲህ አሉ፦ 9‘ክፉ ነገር፥ ሰይፍ ወይም ፍርድ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮሃለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ።’ 10#ዘዳ. 2፥4-19።እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ እስራኤል ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ እንዳይወርሯቸው ያልፈቀድህላቸው፥ ነገር ግን ትተዋቸው ያላጠፉአቸው፥ የአሞንና የሞዓብ ልጆች የሴይርም ተራራ ሰዎች፥ 11እነሆ፥ ለበጎነታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ሊያወጡን መጥተዋል። 12አምላካችን ሆይ! አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን ልንቋቋመው አንችልም፤ ዐይኖቻችን ወደ አንተ ከማንሣት በቀር የምናደርገውን ነገር አናውቅም።” 13የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በጌታ ፊት ቆመው ነበር።
14የጌታም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካርያስ ልጅ በየሕዝኤል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤ 15#ዘዳ. 20፥1-4።እንዲህም አለ፦ “ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ ጌታ እንዲህ ይላችኋል፦ ‘ውግያው የጌታ ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። 16ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ አቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። 17#ዘፀ. 14፥13፤14።እናንተ በዚህ ውግያ ላይ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ! ተሰለፉ፥ ጸንታችሁም ቁሙ፥ የሚሆነውንም የጌታን ድል አድራጊነት እዩ፤’ ጌታም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም በእነርሱ ላይ ውጡ።” 18ኢዮሣፍጥም በግንባሩ ወደ ምድር ሰገደ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በጌታ ፊት በምድር በግንባራቸው ተደፍተው ለጌታ ሰገዱ። 19ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን እጅግ ታላቅ በሆነ ድምፅ ሊያመሰግኑት ቆሙ።
20ማልደውም በመነሣት ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በጌታ እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሳካላችኋል።” 21ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፦ “ጽኑ ፍቅሩ ለዘዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ” የሚሉትንም ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለጌታም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። 22ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሙዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ ጌታ ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተሸነፉ። 23የአሞንና የሞዓብም ልጆችም በሴይርም ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ሊገድሉአቸውና ሊያጠፉአቸውም ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ አንዱ ሌላውን በማገዝ እርስ በርስ ተጠፋፉ።
24የይሁዳም ሰዎች በምድረ በዳ ወዳለው የመጠበቅያ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም። 25ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ለመውሰድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ለመሸከም አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር። 26በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም ጌታን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። 27የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ ጌታ በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። 28በበገናና በመሰንቆ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ጌታ ቤት ገቡ። 29ጌታ የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የጌታር ፍርሃት አደረባቸው። 30የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጠጥታ ሰፈነበት፥ አምላኩም በዙርያው ካሉ አሳረፈው።
የኢዮሣፍጥ አገዛዝ ማብቃቱ
31ኢዮሣፍጥም በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። 32በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 33ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላደረጉም ነበር። 34የቀረውም የፊተኛውና የኋለኛው የኢዮሣፍጥ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ተጽፎአል።
35ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ። 36ኢዮሣፍጥም ወደ ተርሴስ የሚሄዱትን መርከቦች ለመሥራት ከእርሱ ጋር ተባበረ፤ መርከቦቹንም በዔጽዩን-ጋብር አሠሩ። 37የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር፦ “ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና ጌታ ሥራህን አፍርሶታል” ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ለመሄድ አልቻሉም።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ