የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 1:7-17

ትንቢተ ዘካርያስ 1:7-17 አማ05

ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ ሼባጥ የተባለው ዐሥራ አንደኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ የዒዶ የልጅ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ መጣ። የእግዚአብሔር መልአክ በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አየሁ። እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆመ፤ በስተኋላውም ቀይ፥ ሐመርና አምባላይ ፈረሶች ይከተሉት ነበር። እኔም “ጌታዬ ሆይ! እነዚህ ፈረሶች የምን ምሳሌ ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት። እርሱም “የእነዚህ ፈረሶች ምሳሌነት ምን እንደ ሆነ አሳይሃለሁ፤ ምድርን ተዘዋውረው ይቃኙ ዘንድ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” አለኝ። እነርሱም “ምድርን ሁሉ ዞረን መረመርን፤ ምድሪቱ በመላ ሰላም ነች” ብለው ለመልአኩ ነገሩት። መልአኩም “የሠራዊት አምላክ ሆይ! ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ሁሉ ከተቈጣህ እነሆ ሰባ ዓመቶች አለፉ፤ ምሕረት የማታደርግላቸው እስከ መቼ ነው?” ሲል ጠየቀ። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መልስ ሰጠው። ስለዚህም መልአኩ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል እንዲህ ብለህ ዐውጅ አለኝ፥ “እኔ ለተቀደሰችው ከተማዬ ለኢየሩሳሌም ታላቅ ፍቅርና ብርቱ ቅናት አለኝ፤ ሰላም አግኝተው በጸጥታ በሚኖሩ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ እጅግ ተቈጥቼአለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሕዝቤን ከመቅጣት መለስ ባልኩበት ጊዜ እነዚያ የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቤን ከተጠበቀው በላይ አሠቃይተዋል። ስለዚህ ለከተማይቱ ምሕረትን ለማሳየት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ ቤተ መቅደሴና ከተማይቱ እንደገና ታድሰው ይሠራሉ።” መልአኩም እንደገና “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከተሞቹ ተመልሰው እንደሚበለጽጉና ኢየሩሳሌምንም እንደ ጥንቱ እንደሚረዳ የራሱ ከተማም እንደሚያደርጋት ተናገር” አለኝ።