የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘካርያስ 1:7-17

ዘካርያስ 1:7-17 NASV

ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ሳባጥ በሚባለው በዐሥራ አንደኛው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ። በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጧል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም ቀይ፣ ቡናማና ነጭ ፈረሶች ነበሩ። እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁ። ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክም፣ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ። ከዚያም በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው፣ “እነዚህ በምድር ሁሉ እንዲመላለሱ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” ሲል መለሰ። እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት። ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ፣ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ። እግዚአብሔርም ከእኔ ጋራ ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሠኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት። ከዚያም ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤ ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’ “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ በዚያም ቤቴ እንደ ገና ይሠራል፤ መለኪያ ገመድም በኢየሩሳሌም ላይ ይዘረጋል’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”