ትንቢተ ዘካርያስ 1:7-17

ትንቢተ ዘካርያስ 1:7-17 አማ54

በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት ሳባጥ በሚባል በአሥራ አንደኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ እነሆም፥ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ተቀምጦ በሌሊት አየሁ፥ እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ነበር፥ በስተ ኋላውም መጋላና ሐመር አንባላይም ፈረሶች ነበሩ። እኔም፦ ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁ። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ፦ እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ አለኝ። በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረው ሰው፦ እነዚህ በምድር ላይ ይመላለሱ ዘንድ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው ብሎ መለሰ። በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረውን የእግዚአብሔርን መልአክ፦ በምድር ላይ ተመላለስን፥ እነሆም፥ ምድር ሁሉ ዝም ብላ ዐርፋ ተቀምጣለች ብለው መለሱለት። የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ። እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፦ ስበክ እንዲህም በል፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። እኔ ጥቂት ብቻ ተቈጥቼ ሳለሁ እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፥ ባልተቸገሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፥ ቤቴ ይሠራባታል፥ በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል።