ዘካርያስ 1
1
ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ የቀረበ ጥሪ
1ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
2“እግዚአብሔር በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር፤ 3ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ፤’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። 4የቀደሙት ነቢያት፣ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት፣ “ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ” ይላል በማለት ለአባቶቻችሁ ሰብከው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፤’ ይላል እግዚአብሔር። 5አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያትስ ለዘላለም በሕይወት ይኖራሉን? 6ለባሪያዎቼ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃልና ሥርዐት በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሰምን?
“እነርሱም ንስሓ ገብተው እንዲህ አሉ፤ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት በወሰነው መሠረት፣ ለሥራችንና ለመንገዳችን የሚገባውን አድርጎብናል።’ ”
በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው
7ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ሳባጥ በሚባለው በዐሥራ አንደኛው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
8በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ላይ ተቀምጧል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም መጋላ፣ ሐመርና አንባላይ ፈረሶች ነበሩ።
9እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁ።
ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም፣ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ።
10ከዚያም በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው፣ “እነዚህ በምድር ሁሉ እንዲመላለሱ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” ሲል መለሰ። 11እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት።
12ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ፣ “እግዚአብሔር ጸባኦት ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ። 13እግዚአብሔርም ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት።
14ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤ 15ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’
16“ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ በዚያም ቤቴ እንደ ገና ይሠራል፤ መለኪያ ገመድም በኢየሩሳሌም ላይ ይዘረጋል’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።
17“ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”
አራቱ ቀንዶችና አራቱ የእጅ ሙያተኞች
18ከዚያም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ ከፊቴም አራት ቀንዶችን አየሁ፤ 19ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ፣ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት።
እርሱም፣ “እነዚህ ይሁዳን፣ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው” አለኝ።
20ከዚያም እግዚአብሔር አራት የእጅ ሙያተኞችን አሳየኝ። 21እኔም፣ “እነዚህስ ምን ሊያደርጉ መጡ?” አልሁ።
እርሱም፣ “እነዚህ ቀንዶች ማንም ራሱን ቀና ማድረግ እንዳይችል ይሁዳን የበታተኑ ናቸው፤ እነዚህ የእጅ ሙያተኞች ግን የመጡት እነርሱን ሊያስደነግጧቸው፣ ሕዝቡን ለመበታተን በይሁዳ ምድር ላይ ቀንዳቸውን ያነሡትን የእነዚህን የአሕዛብ ቀንዶች ሰብሮ ለመጣል ነው” አለኝ።
Currently Selected:
ዘካርያስ 1: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.