ትንቢተ ዘካርያስ 1
1
እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሕዝቡን መጥራቱ
1ዳርዮስ የፋርስ ንጉሥ በሆነ በሁለተኛው ዓመት፥ በስምንተኛው ወር እግዚአብሔር በዒዶ የልጅ ልጅ በበራክዩ ልጅ በነቢዩ በዘካርያስ አማካይነት የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ #ዕዝ. 4፥24—5፥1፤ 6፥14። 2የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘካርያስን ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ተናገር አለው፦ “እኔ እግዚአብሔር በቀድሞ አባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቼ ነበር፤ 3አሁን ግን እናንተን የምላችሁ ይህ ነው፦ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ። 4እንደ ቀድሞ አባቶቻችሁ አትሁኑ፤ እነርሱን የቀድሞ ነቢያት ‘ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ’ ብለው አስጠንቅቀዋቸው ነበር፤ አባቶቻችሁ ግን ቃሌን አላደመጡም፤ ትእዛዜንም አልጠበቁም። 5የቀድሞ አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያቱስ ለዘለዓለም ይኖራሉን? 6ነገር ግን አገልጋዮቼ በሆኑት በነቢያት አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁ ያስተላለፍኩትን ሕግና ትእዛዝ ባለመጠበቃቸው ተቀጥተው የለምን? ስለዚህ በበደላቸው ተጸጸተው ‘የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ባቀደው መሠረት እንደ ሥራችንና እንደ አካሄዳችን በእኛ ላይ ቅጣትን ማምጣቱ ትክክለኛ ነው’ አሉ።”
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ፈረሶች ያየው ራእይ
7ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ ሼባጥ የተባለው ዐሥራ አንደኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ የዒዶ የልጅ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ መጣ። 8የእግዚአብሔር መልአክ በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አየሁ። እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆመ፤ በስተኋላውም ቀይ፥ ሐመርና አምባላይ ፈረሶች ይከተሉት ነበር። #ራዕ. 6፥2-8። 9እኔም “ጌታዬ ሆይ! እነዚህ ፈረሶች የምን ምሳሌ ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።
እርሱም “የእነዚህ ፈረሶች ምሳሌነት ምን እንደ ሆነ አሳይሃለሁ፤ 10ምድርን ተዘዋውረው ይቃኙ ዘንድ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” አለኝ። 11እነርሱም “ምድርን ሁሉ ዞረን መረመርን፤ ምድሪቱ በመላ ሰላም ነች” ብለው ለመልአኩ ነገሩት።
12መልአኩም “የሠራዊት አምላክ ሆይ! ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ሁሉ ከተቈጣህ እነሆ ሰባ ዓመቶች አለፉ፤ ምሕረት የማታደርግላቸው እስከ መቼ ነው?” ሲል ጠየቀ።
13ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መልስ ሰጠው። 14ስለዚህም መልአኩ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል እንዲህ ብለህ ዐውጅ አለኝ፥ “እኔ ለተቀደሰችው ከተማዬ ለኢየሩሳሌም ታላቅ ፍቅርና ብርቱ ቅናት አለኝ፤ 15ሰላም አግኝተው በጸጥታ በሚኖሩ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ እጅግ ተቈጥቼአለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሕዝቤን ከመቅጣት መለስ ባልኩበት ጊዜ እነዚያ የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቤን ከተጠበቀው በላይ አሠቃይተዋል። 16ስለዚህ ለከተማይቱ ምሕረትን ለማሳየት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ ቤተ መቅደሴና ከተማይቱ እንደገና ታድሰው ይሠራሉ።”
17መልአኩም እንደገና “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከተሞቹ ተመልሰው እንደሚበለጽጉና ኢየሩሳሌምንም እንደ ጥንቱ እንደሚረዳ የራሱ ከተማም እንደሚያደርጋት ተናገር” አለኝ።
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ አራቱ የበሬ ቀንዶች ያየው ራእይ
18በሌላም ራእይ አራት የበሬ ቀንዶችን አየሁ፤ 19ያነጋግረኝ የነበረውንም መልአክ “እነዚህ ቀንዶች የምን ምሳሌ እንደ ሆኑ ንገረኝ” አልኩት።
እርሱም “እነርሱ የይሁዳ፥ የእስራኤልና የኢየሩሳሌም ሕዝቦች እንዲበተኑ ያደረጉ መንግሥታት ናቸው” አለኝ።
20ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር መዶሻ የያዙ አራት አንጥረኞችን አሳየኝ፤ 21እኔም “እነዚህ ሰዎች የመጡት ምን ሊሠሩ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤ እርሱም “እነርሱ የመጡት የይሁዳን ምድር ፈጽሞ አጥፍተው፥ ሕዝብዋ ተበታትኖ እንዲቀር ያደረጉትን የአሕዛብ መንግሥታት ለማሸበርና ለመጣል ነው” አለኝ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 1: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997