የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 2

2
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ መለኪያ ገመድ ያየው ራእይ
1በሌላም ራእይ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰው አየሁ፤ 2እኔም “ወዴት እየሄድክ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤ እርሱም “የኢየሩሳሌም ርዝመትና ስፋት ምን ያኽል እንደ ሆነ ለመለካት መሄዴ ነው” አለኝ።
3ከዚህ በኋላ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወደፊት ሲራመድና ሌላ መልአክም ሊገናኘው ሲመጣ አየሁ። 4የመጀመሪያው መልአክ ሁለተኛውን እንዲህ አለው፦ “የመለኪያ ገመድ ወደያዘው ወጣት በሩጫ ሂድና ‘በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብና ብዙ እንስሶች ስለሚገኙ ትልቅ ግንብ መሥራት ያዳግታል’ ብለህ ንገረው። 5እግዚአብሔር ራሱ በዙሪያዋ እንደ እሳት ቅጽር ሆኖ ከተማይቱን እንደሚጠብቅና በክብሩም በዚያ እንደሚኖር ተስፋ ሰጥቶአል።”
ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለስደተኞች የተደረገ ጥሪ
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በየአራቱም ማእዘን በትኜአችሁ ነበር፤ አሁን ግን ከሰሜን ምድር ተነሥታችሁ ሽሹ። 7በባቢሎን የምትኖሩ እናንተ ስደተኞች ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።” 8እናንተን የሚነካ የእርሱን ዓይን ብሌን እንደሚነካ ሆኖ ይቈጠራል። የክብር ጌታ በበዘበዙአችሁ ሕዝቦች ላይ በላከኝ ጊዜ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው።
9“አሁን እኔ በእነርሱ ላይ እጄን አነሣለሁ፤ እነርሱም ባሪያዎች አድርገው ለገዙአቸው ምርኮኞች ይሆናሉ፤ ከዚያ በኋላ እናንተም የሠራዊት አምላክ እኔን እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10“እኔ መጥቼ በመካከላችሁ ስለምኖር የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ዘምሩ! ደስም ይበላችሁ!” ይላል እግዚአብሔር።
11በዚያን ጊዜ ብዙ የአሕዛብ ነገዶች ከእግዚአብሔር ጋር ተባብረው ወገኖቹ ይሆናሉ። እርሱም በመካከላችሁ ይኖራል፤ እኔንም ወደ እናንተ የላከኝ እርሱ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። 12በተቀደሰችው ምድር ይሁዳን የራሱ ርስት ያደርጋታል፤ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣታል።
13እግዚአብሔር ከተቀደሰ መኖሪያው ለመምጣት ስለ ተነሣ ሁላችሁም በፊቱ ዝም በሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ