የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 119:161-176

መጽሐፈ መዝሙር 119:161-176 አማ05

ባለሥልጣኖች ያለ ምክንያት ያሳድዱኛል፤ እኔ ግን ቃልህን በፍርሃት አከብራለሁ። ብዙ ምርኮ አግኝቶ እንደሚደሰት ሰው በተስፋ ቃልህ እጅግ ደስ ይለኛል። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁም፤ ሕግህን ግን እወዳለሁ። ስለ እውነተኛ ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤ ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ። ትእዛዞችህን እጠብቃለሁ፤ በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ። ትእዛዞችህንና ሕግህን አከብራለሁ፤ የምሠራውንም ሁሉ አንተ ታያለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። ሕግህን ስለምታስተምረኝ ዘወትር አመሰግንሃለሁ። ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ። ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥ እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤ በሕግህም ደስ ይለኛል። አንተን ለማመስገን እንድችል ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤ ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤ ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥ እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።