የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 119

119
አሌፍ
የእግዚአብሔር ሕግ
1በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፥
በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት የሚኖሩ ሰዎች
የተባረኩ ናቸው።
2ትእዛዞቹን የሚጠብቁ፥
በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት፥
የተባረኩ ናቸው።
3የማይሳሳቱና በእግዚአብሔር መንገድ
የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።
4እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሕጎችህን ሰጥተኸናል፤
በታማኝነት እንድንታዘዛቸውም ነግረኸናል፤
5ድንጋጌህን በመጠበቅ ታማኝ ለመሆን
በብርቱ እመኛለሁ።
6ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ
ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም።
7የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን
በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ።
8ሕግህን ስለምፈጽም
ፈጽሞ አትተወኝ።
ቤት
ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ
9ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት
ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው።
10አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ
ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ።
11አንተን እንዳልበድል
ቃልህን በልቤ አኖራለሁ።
12እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤
የአንተን ሕግ አስተምረኝ።
13አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ
መላልሼ አነባለሁ።
14የአንተን ትእዛዝ መፈጸም
ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል።
15ሥርዓትህን አጠናለሁ፤
በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ።
16በሕግህ ደስ ይለኛል፤
ቃልህንም አልረሳም።
ጋሜል
ከእግዚአብሔር ሕግ የሚገኝ ደስታ
17በሕይወት እንድኖርና የቃልህን ትምህርት እንድጠብቅ
ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ።
18በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት
ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ።
19እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤
ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ።
20ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት
ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች።
21የተረገሙትንና ከትእዛዞችህ የሚያፈነግጡትን
ትዕቢተኞች ትገሥጻለህ።
22እኔ ሕግህን ስለ ጠበቅሁ
ስድባቸውንና ንቀታቸውን ከእኔ አርቅልኝ።
23መሪዎች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ
እኔ አገልጋይህ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ።
24ትእዛዞችህ ያስደስቱኛል፤
መካሪዎቼም እነርሱ ናቸው።
ዳሌጥ
የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈጸም መወሰን
25ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤
በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት
ሕይወቴን አድስልኝ።
26አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤
አንተም ሰማኸኝ፤
እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ።
27ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤
እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
28ሐዘን በርትቶብኛል፤
በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ኀይሌን አድስልኝ።
29ሐሰትን ከእኔ አርቅልኝ፤
በቸርነትህም ሕግህን አስተምረኝ።
30ታማኝ ለመሆንና
ሕግህን ለመጠበቅ ወስኜአለሁ።
31እግዚአብሔር ሆይ!
በሕግህ ጸንቼአለሁ፤
እባክህ አታሳፍረኝ።
32ብዙ ማስተዋልን ስለ ሰጠኸኝ፤
ትእዛዞችህን በትጋት እፈጽማለሁ።
ማስተዋል ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
33እግዚአብሔር ሆይ! የሕግህን ትርጒም አስተምረኝ፤
እኔም ዘወትር እከተለዋለሁ።
34ሕግህን ግለጥልኝ፤ እኔም አከብረዋለሁ፤
በሙሉ ልቤም እጠብቀዋለሁ።
35ትእዛዞችህ ስለሚያስደስቱኝ
እንድፈጽማቸው እርዳኝ።
36ሀብት ለማግኘት ከመስገብገብ ይልቅ
ሕግህን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርግ።
37ወደ ከንቱ ነገር ከማዘንበል ጠብቀኝ፤
በቃልህ መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ።
38ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ
የሰጠኸውን የተስፋ ቃል ፈጽም።
39ፍርድህ ትክክል ስለ ሆነ
ከምፈራው ውርደት ጠብቀኝ።
40ትእዛዞችህን መጠበቅ እመኛለሁ፤
አንተ እውነተኛ ስለ ሆንክ ሕይወቴን አድስልኝ።
ዋው
በእግዚአብሔር ሕግ መደገፍ
41እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤
በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ።
42በቃልህ ስለምተማመን
ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ።
43ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ
ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ።
44ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ።
45ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ
በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ።
46ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤
ከቶም አላፍርም።
47በትእዛዞችህ የምደሰተው
እነርሱን ስለምወዳቸው ነው።
48የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤
ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ።
ዛይ
በእግዚአብሔር ሕግ መታመን
49ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ
ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ።
50የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥
በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ።
51ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤
እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም።
52እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ
ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ።
53ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ
በብርቱ ተቈጣሁ።
54በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ
የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው።
55እግዚአብሔር ሆይ!
በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤
በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ።
56ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥
በረከትን አገኘሁ።
ሔት
ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ
57እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤
ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ።
58በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ
ከልብ እለምንሃለሁ።
59አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ
ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ።
60ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ።
61ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም
እኔ ግን ሕግህን አልረሳም።
62ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን
በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ።
63አንተን የሚፈሩትንና
ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ።
64እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤
ሕጎችህን አስተምረኝ።
ጤት
የእግዚአብሔር ሕግ ክቡርነት
65እግዚአብሔር ሆይ! የተስፋ ቃልህን ጠብቀሃል፤
ለእኔም ለአገልጋይህ ቸር ሆነሃል።
66በትእዛዞችህ ስለምተማመን
አስተዋይነትንና ዕውቀትን ስጠኝ።
67አንተ እኔን ከመቅጣትህ በፊት እሳሳት ነበር፤
አሁን ግን ለቃልህ እታዘዛለሁ።
68አንተ ቸር ስለ ሆንክ ቸር የሆነውን ታደርጋለህ፤
ሕጎችህን አስተምረኝ።
69ምንም እንኳ ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ቢያጠፉ
እኔ ትእዛዞችህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ።
70እነርሱ ትዕቢተኞችና ስሜተ ቢሶች ናቸው፤
እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።
71ሕግህን እንድማር ስላደረገኝ
መቀጣቴ መልካም ሆነልኝ።
72ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ይልቅ
ለእኔ እጅግ ዋጋ ያለው
አንተ የምትሰጠው ሕግ ነው።
ዮድ
የእግዚአብሔር ሕግ ትክክለኛነት
73እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤
ትእዛዞችህን እማር ዘንድ አስተዋይነትን ስጠኝ።
74በተስፋ ቃልህ ስለምታመን
አንተን የሚያከብሩ ሁሉ እኔን በሚያዩበት ጊዜ ደስ ይበላቸው።
75እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤
የቀጣኸኝም እውነተኛ በመሆንህ ነው።
76ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት
ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ያጽናናኝ።
77በሕግህ ደስ ስለሚለኝ
ሕያው ሆኜ ለመኖር እችል ዘንድ
ርኅራኄ አድርግልኝ።
78በሐሰት ያለምክንያት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ፤
እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ።
79አንተን የሚፈሩ ትእዛዞችህን ያውቁ ዘንድ
ወደ እኔ ይምጡ።
80ኀፍረት እንዳይደርስብኝ
ሕግህን በትክክል እንድፈጽም እርዳኝ።
ካፍ
መዳንን ለማግኘት የቀረበ ጸሎት
81የአንተን አዳኝነት በሙሉ ልቤ እመኛለሁ።
እምነቴን በቃልህ ላይ አድርጌአለሁ።
82“መቼ ታጽናናኝ ይሆን?” ብዬ
የተስፋ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ።
83ጢስ በሚጤስበት ቤት ተሰቅሎ
እንደ ተጨማደደ የወይን ጠጅ አቊማዳ
ከጥቅም ውጪ ሆኜአለሁ፤
ይህም ሁሉ ሆኖ ሕግህን አልረሳሁም።
84እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቈይ?
የሚያሳድዱኝንስ የምትቀጣቸው መቼ ነው?
85ሕግህን የማይጠብቁ ትዕቢተኞች
እኔን ለማጥመድ ጒድጓድ ቆፍረዋል።
86ትእዛዞችህ ሁሉ የጸኑ ናቸው፤
ያለ ምክንያት ስለሚያሳድዱኝ እርዳኝ!
87እነርሱ ሊገድሉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤
እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልኩም።
88ሕግህን እጠብቅ ዘንድ
በዘለዓለማዊ ፍቅርህ ሕይወትን ስጠኝ።
ላሜድ
በእግዚአብሔር ሕግ መታመን
89እግዚአብሔር ሆይ! ቃልህ ዘለዓለማዊ ነው፤
በሰማይም ጸንቶ ይኖራል።
90ቃልህ በዘመናት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤
ምድርን መሠረትካት፤
ጸንታም ትኖራለች።
91ፍጥረቶች ሁሉ አገልጋዮችህ ስለ ሆኑ
ትእዛዞችህ እስከ ዛሬ ጸንተው ቈይተዋል።
92ሕግህ የደስታዬ ምንጭ ባይሆን ኖሮ
ከሥቃዬ የተነሣ በሞትኩ ነበር።
93በሕግህ አማካይነት በሕይወት እንድኖር ጠብቀኸኛልና
ሕግህን ከቶ አልረሳም።
94እኔ የአንተ ስለ ሆንኩ አድነኝ!
ትእዛዞችህንም ለማክበር እፈልጋለሁ።
95ክፉዎች እኔን ለመግደል ያደባሉ፤
እኔ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ።
96የሁሉም ነገር ፍጹምነት ወሰን አለው፤
የትእዛዞችህ ፍጹምነት ግን ወሰን የለውም።
ሜም
የእግዚአብሔርን ሕግ መውደድ
97ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤
ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ።
98ትእዛዝህ መቼም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ፥
ከጠላቶቼ ሁሉ ይልቅ እኔን አስተዋይ ያደርገኛል።
99ሕግህን ዘወትር ስለማሰላስል፥
ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥበብ አለኝ።
100ትእዛዞችህን ሁሉ ስለምፈጽም፥
ከሽማግሌዎች ሁሉ የበለጠ አስተዋይነት አለኝ።
101ለቃልህ መታዘዝ ስለምፈልግ፥
መጥፎ ጠባይን ሁሉ አስወግጄአለሁ።
102ያስተማርከኝ አንተ ስለ ሆንክ
ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም።
103ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው!
ከማር ወለላ ይልቅ ይጣፍጣል።
104ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቼአለሁ፤
ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ።
ኖን
ከእግዚአብሔር ሕግ የሚገኝ ብርሃን
105ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤
ለመንገዴም ብርሃን ነው።
106እውነተኛ ትእዛዞችህን ለመጠበቅ
በመሐላ የገባሁትን ቃል አጸናለሁ።
107እግዚአብሔር ሆይ! ሥቃዬ እጅግ ከባድ ስለ ሆነ
በተስፋ ቃልህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ።
108እግዚአብሔር ሆይ! የምስጋና ጸሎቴን ተቀበል፤
ትእዛዞችህንም አስተምረኝ።
109ሕይወቴ በአደጋ ላይ ቢሆንም እንኳ
ሕግህን አልረሳም
110ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤
እኔ ግን ከትእዛዞችህ ፈቀቅ አላልኩም።
111ሕግህ ዘለዓለማዊ ሀብቴ ነው፤
የልቤም ደስታ እርሱ ነው።
112እስከምሞትበት ቀን ድረስ
ሕጎችህን ለመፈጸም ወስኜአለሁ፤
ሳምኬት
በእግዚአብሔር ሕግ የሚገኝ ዋስትና
113በፍጹም ልባቸው በአንተ የማይታመኑትን ወላዋዮች ሁሉ ጠላሁ፤
ሕግህን ግን ወደድኩ።
114አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያዬ ነህ፤
በቃልህ ተስፋ አደርጋለሁ።
115እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ፤
እኔ የአምላኬን ትእዛዞች መጠበቅ እፈልጋለሁ።
116በሕይወት እኖር ዘንድ በተስፋ ቃልህ መሠረት አበርታኝ!
ተስፋዬንም አታጨልምብኝ!
117እድን ዘንድ ደግፈኝ፤
ሁልጊዜም ሕጎችህን እፈጽማለሁ።
118ዕቅዳቸው ተንኰልና ሐሰት የሞላበት በመሆኑ፥
ከሕግህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ታስወግዳቸዋለህ።
119ክፉዎችን ሁሉ እንደ ቆሻሻ ነገር ታስወግዳቸዋለህ፤
ስለዚህ ሥርዓትህን እወዳለሁ።
120አንተን ከመፍራቴ የተነሣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፤
ፍርድህንም እጅግ ፈራሁት።
ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ
121ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጌአለሁ፤
ስለዚህ ለሚጨቊኑኝ ጠላቶቼ አትተወኝ!
122የእኔን የአገልጋይህን ደኅንነት አረጋግጥ፤
እብሪተኞች እንዲያጠቁኝ አታድርግ።
123አዳኝነትህንና እውነተኛ ቃል ኪዳንህን በመጠባበቅ
ዐይኖቼ ደከሙ።
124ለእኔ ለአገልጋይህ ፍቅርህን አሳይ፤
ሕጎችህንም አስተምረኝ።
125እኔ አገልጋይህ ነኝ፤
ሥርዓትህንም እንዳውቅ ማስተዋልን ስጠኝ።
126እግዚአብሔር ሆይ! ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ
ፍርድህን የምትገልጥበት ጊዜው አሁን ነው።
127ትእዛዞችህን ከወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ፤
አዎ፥ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ አብልጬ እወዳለሁ።
128የአንተ ትእዛዞች ትክክል መሆናቸውን ስለማምን
የሐሰትን መንገድ ሁሉ እጠላለሁ።
የእግዚአብሔርን ሕግ ለማክበር መመኘት
129ሥርዓቶችህ አስደናቂዎች ናቸው፤
እኔም በሙሉ ልቤ እታዘዛቸዋለሁ።
130የቃልህ ትርጒም ብርሃን ይሰጣል፤
ሞኞችን አስተዋዮች ያደርጋል።
131ትእዛዞችህን በጣም ከመናፈቄ የተነሣ
አፌን በጒጒት እከፍታለሁ።
132ወደ እኔ ተመለስ፤
ለሚወዱህ ሁሉ እንደምታደርገውም ምሕረት አድርግልኝ።
133በተስፋ ቃልህ መሠረት አካሄዴን አስተካክል፤
ስሕተትም እንዲሠለጥንብኝ አታድርግ።
134ትእዛዞችህን መጠበቅ እንድችል
ከሚጨቊኑኝ ሰዎች እጅ አድነኝ።
135የፊትህን ብርሃን ለባሪያህ አብራለት፤
ሕግህንም አስተምረኝ።
136ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ
እንባዬ እንደ ወንዝ ውሃ ይፈስሳል።
ጻዴ
የእግዚአብሔር ሕግ ትክክለኛነት
137እግዚአብሔር ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤
ፍርድህም ቅን ነው።
138ሕግህ በፍጹም እውነትና ትክክል ነው።
139ጠላቶቼ ትእዛዞችህን አለመቀበላቸው
በጣም ያበሳጨኛል።
140የተስፋ ቃልህ እጅግ የታመነ ነው፤
እኔም በጣም እወደዋለሁ።
141እኔ የማልጠቅምና የተናቅሁ ብሆንም እንኳ
ሥርዓትህን አልዘነጋሁም።
142ጽድቅህ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤
ሕግህም ዘለዓለማዊ እውነት ነው።
143ብዙ ችግርና ጭንቀት ደርሶብኛል፤
ትእዛዞችህ ግን ደስታን ይሰጡኛል።
144ሥርዓትህ ዘወትር ትክክል ነው፤
በሕይወት ለመኖር እንድችል ማስተዋልን ስጠኝ።
ቆፍ
ከጠላት እጅ ለመዳን የቀረበ ጸሎት
145እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ፤
ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ስማኝ፤
እኔም ሕጎችህን እፈጽማለሁ።
146ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አድነኝም፤
እኔም ሕግህን እጠብቃለሁ።
147ጎህ ከመቅደዱ በፊት
ርዳታህን በመፈለግ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤
በገባህልኝም ቃል ተስፋ አደርጋለሁ።
148ቃልህን በማሰላሰል ለማጥናት
ሌሊቱን ሙሉ እነቃለሁ።
149እግዚአብሔር ሆይ!
ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ስማኝ!
በትእዛዝህ መሠረት ሕይወቴን ጠብቅ!
150ሕግህን የማያከብሩ፥ ክፉ ዕቅድ ዐቅደው የሚያሳድዱኝ ሰዎች
ወደ እኔ ቀርበዋል።
151እግዚአብሔር ሆይ!
አንተ ግን ለእኔ ቅርብ ነህ፤
ትእዛዞችህ ሁሉ እውነተኞች ናቸው።
152ሕጎችህን በማጥናት ለዘለዓለም እንዲጸኑ ያደረግሃቸው መሆናቸውን
ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድቼአለሁ።
ሬስ
ወደ እግዚአብሔር መማጸን
153እኔ ሕግህን አልረሳሁም፤
ስለዚህ ችግሬን ተመልክተህ አድነኝ።
154ስለ መብቴ ተከራከርልኝ፤ አድነኝ፤
በተስፋ ቃልህም መሠረት በሕይወት አኑረኝ።
155ሕግህን ስለማይፈልጉ
ክፉዎች የመዳን ተስፋ የላቸውም።
156እግዚአብሔር ሆይ! ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤
በትእዛዝህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ!
157የሚጠሉኝና የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው፤
እኔ ግን ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም።
158ቃልህን ስለማይጠብቁ፥
ከሐዲዎችን አይቼ ተጸየፍኳቸው።
159እግዚአብሔር ሆይ!
ትእዛዞችህን እንደምወድ ተመልከት፤
ስለዚህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ በሕይወት አኑረኝ!
160ቃልህ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ነው፤
ትክክለኛ ፍርድህም ዘለዓለማዊ ነው።
ሳን
ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ
161ባለሥልጣኖች ያለ ምክንያት ያሳድዱኛል፤
እኔ ግን ቃልህን በፍርሃት አከብራለሁ።
162ብዙ ምርኮ አግኝቶ እንደሚደሰት ሰው
በተስፋ ቃልህ እጅግ ደስ ይለኛል።
163ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁም፤
ሕግህን ግን እወዳለሁ።
164ስለ እውነተኛ ፍርድህ
በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ።
165ሕግህን የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤
ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም።
166እግዚአብሔር ሆይ!
አዳኝነትህን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤
ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ።
167ትእዛዞችህን እጠብቃለሁ፤
በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ።
168ትእዛዞችህንና ሕግህን አከብራለሁ፤
የምሠራውንም ሁሉ አንተ ታያለህ።
ታው
ርዳታ ለማግኘት የሚቀርብ ጸሎት
169እግዚአብሔር ሆይ!
ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤
በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ።
170ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤
በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ።
171ሕግህን ስለምታስተምረኝ
ዘወትር አመሰግንሃለሁ።
172ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥
ስለ ቃልህ እዘምራለሁ።
173ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥
እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን።
174እግዚአብሔር ሆይ!
አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤
በሕግህም ደስ ይለኛል።
175አንተን ለማመስገን እንድችል
ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤
ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን።
176እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤
ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥
እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ