የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 119:161-176

መዝሙር 119:161-176 NASV

ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ። ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣ በቃልህ ደስ አለኝ። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፣ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ። ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤ እጅግ እወድደዋለሁና። መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ታደገኝ። ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ። ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር። ትእዛዝህን መርጫለሁና፣ እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ደስታዬ ነው። አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ ሕግህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣ ባሪያህን ፈልገው።