የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 119:161-176

መዝሙር 119:161-176 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ። ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣ በቃልህ ደስ አለኝ። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ። ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፣ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ። ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤ እጅግ እወድደዋለሁና። መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤ እንደ ቃልህም ታደገኝ። ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ። ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር። ትእዛዝህን መርጫለሁና፣ እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ደስታዬ ነው። አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ ሕግህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣ ባሪያህን ፈልገው።

መዝሙር 119:161-176 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ባለሥልጣኖች ያለ ምክንያት ያሳድዱኛል፤ እኔ ግን ቃልህን በፍርሃት አከብራለሁ። ብዙ ምርኮ አግኝቶ እንደሚደሰት ሰው በተስፋ ቃልህ እጅግ ደስ ይለኛል። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁም፤ ሕግህን ግን እወዳለሁ። ስለ እውነተኛ ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤ ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ። ትእዛዞችህን እጠብቃለሁ፤ በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ። ትእዛዞችህንና ሕግህን አከብራለሁ፤ የምሠራውንም ሁሉ አንተ ታያለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። ሕግህን ስለምታስተምረኝ ዘወትር አመሰግንሃለሁ። ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ። ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥ እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤ በሕግህም ደስ ይለኛል። አንተን ለማመስገን እንድችል ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤ ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤ ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥ እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።

መዝሙር 119:161-176 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ፥ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ። ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ። ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፥ ሕግህን ግን ወደድሁ። ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም። አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደርግሁ፥ ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ። ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው። መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፥ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ። ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፥ እንደ ቃልህ አድነኝ። ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ። ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ። ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን። አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፥ ሕግህም ተድላዬ ነው። ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፥ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባርያህን ፈልገው።