“ነዶአችሁን ለእግዚአብሔር በመወዝወዝ የሚቀርብ ልዩ መባ አድርጋችሁ ካመጣችሁበት ሰንበት ማግስት ጀምሮ ሰባት ሳምንት ቊጠሩ፤ ከሰባተኛው ሰንበት በኋላ በኀምሳኛው ቀን እንደገና የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ ሁለት እንጀራ በመወዝወዝ ልዩ መባ አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ እያንዳንዱ እንጀራ እርሾ ገብቶበት ከሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት ጋር ተጋግሮ ስለሚሰበሰበው አዲስ መከር ለእግዚአብሔር የበኲራት መባ ሆኖ ይቅረብ። ከእንጀራውም ጋር ማኅበሩ ምንም ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰባት የበግ ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ያምጡ፤ እነርሱም ከእህሉ ቊርባንና ከወይን ጠጁ መባ ጋር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት ሆነው ይቀርባሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ከዚያም ቀጥሎ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አንድ ተባዕት ፍየል፤ ለአንድነት መሥዋዕት የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ካህኑም ከበኲራቱ እንጀራ ከሁለቱ ጠቦቶች ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ እርሱም የካህናቱ ድርሻ ሆኖ ይነሣል፤ እነዚህም ስጦታዎች የተቀደሱ ናቸው። በዚያም ቀን የአምልኮ ስብሰባ እንዲሆንላችሁ ታውጃላችሁ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ይህ በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። “የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ ለመሰብሰብ ወደ ኋላ አትመለሱ፤ እርሱን ለድኾችና ለመጻተኞች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔርን ለማምለክ በመለከት የታወጀ መታሰቢያ የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ። በዚያን ዕለት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡበት እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛው ቀን የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረያ ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው፤ በዚያን ዕለት እግዚአብሔርን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ ለንስሓም ሰውነታችሁን አዋርዱ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የሕዝቡን ኃጢአት የማስወገድ ሥርዓት የሚፈጸምበት ዕለት ስለ ሆነ፥ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት። በዚያን ዕለት በንስሓ ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ በዚያን ዕለት ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ቢኖር ከሕዝብ ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ ስለዚህ በዚያን ዕለት ምንም ሥራ እንዳትሠሩ፤ ይህም የሥርዓት መመሪያ በምትኖሩበት ቦታ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኖራል። ወሩ ከገባ ከዘጠነኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዐሥረኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ጊዜ ድረስ ለንስሓ ራሳችሁን አዋርዱ፤ ይህን ዕለት ልዩ የዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ጠብቁት።”
ኦሪት ዘሌዋውያን 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 23:15-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች