“ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቍጠሩ። እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ ዐምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር አምጡ። ከእንጀራውም ጋራ ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት እንከን የሌለው ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ። ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋራ የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው። በዚያ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው። “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በመለከት ድምፅም የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ። መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለ ሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ። በዚያ ዕለት ሰውነቱን የማያጐሳቍል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው። ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።”
ዘሌዋውያን 23 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘሌዋውያን 23
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘሌዋውያን 23:15-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች