ዘሌዋውያን 23:15-32
ዘሌዋውያን 23:15-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ያቀረባችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ሱባዔ ቍጠሩ፤ እስከ መጨረሻዋ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም የስንዴ ዱቄት የተሠራ ሁለት የቍርባን እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ከእህላችሁ ቀዳምያት ለእግዚአብሔር በእርሾ ይጋገራል። ከኅብስቱም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ ከመንጋውም አንድ ወይፈን፥ ሁለትም ነውር የሌለባቸው አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው መሥዋዕት እንዲሆን መሥዋዕታቸውና ቍርባናቸው፥ ወይናቸውም ለእግዚአብሔር ይሁን። አንድም አውራ ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ከመጀመሪያው የእህል ቍርባን ጋር ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። ካህኑም ከበኵራቱ ኅብስት፥ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለቍርባን ያቅርበው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ላቀረበው ለካህኑ ይሁን። ያችንም ቀን ቅድስት ጉባኤ ብላችሁ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው። “የምድራችሁን መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ በእርሻችሁ የቀረውን አጥርታችሁ አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰች ጉባኤ ትሁንላችሁ። የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛዋ ቀን የማስተስረያ ቀን ናት፤ ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቋት፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እናንተ ማስተስረያ ትሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ናትና በዚያች ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት። በዚያችም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። በዚያችም ቀን ሥራ የሚሠራ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሕግ ነው። የዕረፍት ሰንበት ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምራችሁ እስከ ዐሥረኛው ቀን ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ።”
ዘሌዋውያን 23:15-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቍጠሩ። እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ ዐምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር አምጡ። ከእንጀራውም ጋራ ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት እንከን የሌለው ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ። ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋራ የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው። በዚያ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው። “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በመለከት ድምፅም የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ። መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለ ሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ። በዚያ ዕለት ሰውነቱን የማያጐሳቍል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው። ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።”
ዘሌዋውያን 23:15-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ፤ እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ለበኵራት ቍርባን እንዲሆን በእርሾ ይጋገራል። ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሁኑ፤ ከእህልም ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሁኑ። አንድም አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። ካህኑም ከበኵራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዛቸዋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ለካህኑ ይሁን። በዚያም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችሁ ዘንድ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ። የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቍት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፥ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ።
ዘሌዋውያን 23:15-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ነዶአችሁን ለእግዚአብሔር በመወዝወዝ የሚቀርብ ልዩ መባ አድርጋችሁ ካመጣችሁበት ሰንበት ማግስት ጀምሮ ሰባት ሳምንት ቊጠሩ፤ ከሰባተኛው ሰንበት በኋላ በኀምሳኛው ቀን እንደገና የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ ሁለት እንጀራ በመወዝወዝ ልዩ መባ አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ እያንዳንዱ እንጀራ እርሾ ገብቶበት ከሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት ጋር ተጋግሮ ስለሚሰበሰበው አዲስ መከር ለእግዚአብሔር የበኲራት መባ ሆኖ ይቅረብ። ከእንጀራውም ጋር ማኅበሩ ምንም ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰባት የበግ ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ያምጡ፤ እነርሱም ከእህሉ ቊርባንና ከወይን ጠጁ መባ ጋር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት ሆነው ይቀርባሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ከዚያም ቀጥሎ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አንድ ተባዕት ፍየል፤ ለአንድነት መሥዋዕት የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ካህኑም ከበኲራቱ እንጀራ ከሁለቱ ጠቦቶች ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ እርሱም የካህናቱ ድርሻ ሆኖ ይነሣል፤ እነዚህም ስጦታዎች የተቀደሱ ናቸው። በዚያም ቀን የአምልኮ ስብሰባ እንዲሆንላችሁ ታውጃላችሁ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ይህ በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። “የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ ለመሰብሰብ ወደ ኋላ አትመለሱ፤ እርሱን ለድኾችና ለመጻተኞች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔርን ለማምለክ በመለከት የታወጀ መታሰቢያ የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ። በዚያን ዕለት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡበት እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛው ቀን የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረያ ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው፤ በዚያን ዕለት እግዚአብሔርን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ ለንስሓም ሰውነታችሁን አዋርዱ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የሕዝቡን ኃጢአት የማስወገድ ሥርዓት የሚፈጸምበት ዕለት ስለ ሆነ፥ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት። በዚያን ዕለት በንስሓ ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ በዚያን ዕለት ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ቢኖር ከሕዝብ ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ ስለዚህ በዚያን ዕለት ምንም ሥራ እንዳትሠሩ፤ ይህም የሥርዓት መመሪያ በምትኖሩበት ቦታ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኖራል። ወሩ ከገባ ከዘጠነኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዐሥረኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ጊዜ ድረስ ለንስሓ ራሳችሁን አዋርዱ፤ ይህን ዕለት ልዩ የዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ጠብቁት።”
ዘሌዋውያን 23:15-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ለመወዝወዝ ቁርባን ነዶውን ካመጣችሁበት ቀን ከሰንበት በኋላ በማግስቱ ያሉትን ቀኖች ቁጠሩ። እነርሱም ሰባት ሙሉ ሳምንታት ይሁኑ። እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ ኀምሳ ቀን ቁጠሩ። ከዚያም አዲሱን የእህል ቁርባን ለጌታ አቅርቡ። ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ። ለጌታ ለበኵራት ቁርባን እንዲሆን በእርሾ ተቦክቶ ይጋገራል። ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ተባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ሆኖ ከእህል ቁርባናቸውና ከመጠጥ ቁርባናቸው ጋር ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ። እንዲሁም አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለአንድነት መሥዋዕት አቅርቡ። ካህኑም ከበኩራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ይወዘውዛቸዋል። ለካህኑ ለጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ። በዚያም ቀን ታውጃላችሁ፤ የተቀደሰ ጉባኤም ታደርጋላችሁ። የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። “የምድራችሁንም መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ እስከ እርሻችሁ ድንበር ድረስ ፈጽማችሁ አትሰብስቡ። የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሀውና ለእንግዳው ተዉት። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን ፈጽሞ የምታርፉበት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የምታውጁበት፥ የተቀደሰ ጉባኤ የምታደርጉበት ይሁንላችሁ። የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ራሳችሁን አዋርዱ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ። በአምላካችሁም በጌታ ፊት ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። በዚያም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። በዚያም ቀን ማናቸውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምሮ፥ ከማታ እስከ ማታ ድረስ ሰንበታችሁን አድርጉ።”