ኦሪት ዘሌዋውያን 23
23
የሃይማኖት በዓላት
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ቅዱሳት ጉባኤያት ብላችሁ የምትጠሩአቸው በዓላቴ፥ የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 3ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። 4እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሱ ጉባኤያት ናቸው።
በዓለ ፋሲካና በዓለ ናዕት
(ዘኍ. 28፥16-25)
5“በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚእብሔር ፋሲካ ነው። 6በዚህም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ ብሉ። 7መጀመሪያይቱ ቀን ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩባት። 8ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ሰባተኛዋ ቀን ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩባት።”
9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ መከሩንም ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ 11እርሱም ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ያቀርበዋል፤ በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ካህኑ ያቅርበው፤ 12ነዶውንም ባቀረባችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 13የስንዴም ቍርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው ቍርባን ይሁን፤ የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን። 14እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት የአምላካችሁን ቍርባን እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው።
በዓለ ሠዊት
(ዘኍ. 28፥26-31)
15“ያቀረባችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ሱባዔ ቍጠሩ፤ 16እስከ መጨረሻዋ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 17ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም የስንዴ ዱቄት የተሠራ ሁለት የቍርባን እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ከእህላችሁ ቀዳምያት ለእግዚአብሔር በእርሾ ይጋገራል። 18ከኅብስቱም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ ከመንጋውም አንድ ወይፈን፥ ሁለትም ነውር የሌለባቸው አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው መሥዋዕት እንዲሆን መሥዋዕታቸውና ቍርባናቸው፥ ወይናቸውም ለእግዚአብሔር ይሁን። 19አንድም አውራ ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ከመጀመሪያው የእህል ቍርባን ጋር ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። 20ካህኑም ከበኵራቱ ኅብስት፥ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለቍርባን ያቅርበው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ላቀረበው ለካህኑ ይሁን። 21ያችንም ቀን ቅድስት ጉባኤ ብላችሁ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው።
22“የምድራችሁን መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ በእርሻችሁ የቀረውን አጥርታችሁ አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።”
በዓለ መጥቅዕ
(ዘኍ. 29፥1-6)
23እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰች ጉባኤ ትሁንላችሁ። 25የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ።”
ዕለተ አስተስርዮ
(ዘኍ. 29፥7-11)
26እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 27“በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛዋ ቀን የማስተስረያ ቀን ናት፤ ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቋት፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። 28በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እናንተ ማስተስረያ ትሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ናትና በዚያች ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት። 29በዚያችም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 30በዚያችም ቀን ሥራ የሚሠራ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። 31ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሕግ ነው። 32የዕረፍት ሰንበት ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምራችሁ እስከ ዐሥረኛው ቀን ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ።”
የዳስ በዓል
(ዘኍ. 29፥12-40)
33እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 34“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። 35የመጀመሪያዋ ቀን ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት። 36ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ስምንተኛዋም ቀን የተቀደሰች ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቡ፤ የመሰናበቻ በዓል ነውና፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
37“የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ በዓላት እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38እነዚህም ከእግዚአብሔር ሰንበታት ሌላ፥ ለእግዚአብሔርም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለቶቻችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው። 39ከሰባተኛውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ታደርጋላችሁ፤ የመጀመሪያዋ ቀን ዕረፍት ትሁን፤ ስምንተኛዋም ቀን ዕረፍት ትሁን። 40በመጀመሪያዋ ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባውንም ቅርንጫፍ፥ የለመለመውንም ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት በየዓመቱ ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። 41በየዓመቱ በሰባተኛው ወር ይህን በዓል ታደርጉ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሕግ ይሁንላችሁ። 42ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ 43ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የሀገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።” 44ሙሴም የጌታን የእግዚአብሔርን በዓላት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ተናገረ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 23: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ