የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 23

23
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው። 3ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። 4እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሰ ጉባኤ ናቸው። 5በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። 6በዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብሉ። 7በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 8ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ መከሩንም ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ 11እርሱም ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ካህኑ ይወዝውዘው። 12ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። 13የእህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ይሁን፤ የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን። 14እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት የአምላካችሁን ቍርባን እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። 15የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ፤ 16እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። 17ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ለበኵራት ቍርባን እንዲሆን በእርሾ ይጋገራል። 18ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሁኑ፤ ከእህልም ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሁኑ። 19አንድም አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። 20ካህኑም ከበኵራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዛቸዋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ለካህኑ ይሁን። 21በዚያም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችሁ ዘንድ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። 22የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 23እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ። 25የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። 26እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 27በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቍት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። 28በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። 29በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 30በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። 31ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። 32የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፥ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ። 33እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 34ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከአሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። 35በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። 36ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን ቍርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። 37የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የእሳት ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38እነዚህም ከእግዚአብሔር ሰንበታት ሌላ፥ ለእግዚአብሔርም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው። 39ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። 40በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የሰሌን ቅርንጫፍ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። 41ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው፤ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። 42-43ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የአገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 44ሙሴም የእግዚአብሔርን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ