የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 24

24
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2መብራቱን ሁልጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 3በምስክሩ መጋረጃ ውጭ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ያሰናዳው፤ ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። 4በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያሰናዳቸው። 5መልካሙንም ዱቄት ወስደህ አሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን። 6እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ ገበታ ላይ አኑራቸው። 7ለእግዚአብሔርም ለእሳት ቍርባን በእንጀራው ላይ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሁለቱ ተርታ ላይ ጥሩ ዕጣን አድርግ። 8በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያድርገው፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። 9ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን በዘላለም ሥርዓት ለእርሱ ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት። 10አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ተጣሉ፤ 11የእስራኤላዊቱም ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። 12ከእግዚአብሔርም አፍ ስለ እርሱ ፍርድ እስኪወጣላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት። 13እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 14ተሳዳቢውን ከሰፈሩ ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው። 15ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ፦ ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል። 16የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል። 17ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። 18እንስሳንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይክፈል። 19ሰውም ባልንጀራውን ቢጐዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። 20ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት። 21እንስሳውንም የሚገድል ካሣ ይተካ፤ ሰውንም የሚገድል ይገደል። 22እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይሁንላችሁ። 23ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ