“የራእይ ሸለቆ” ተብሎ ስለሚጠራው ቦታ የተነገረ ቃል ይህ ነው፤ በየቤታችሁ ሰገነት ላይ ሆናችሁ በዓል የምታከብሩት በምን ምክንያት ነው? በሁካታና በጩኸት የተሞላሽ አንቺ ከተማ ሆይ! ሰክረው በመንገዶችሽ ላይ የወደቁት ሰዎች በሰይፍ የተገደሉ ወይም በጦርነት የሞቱ አይደሉም። መሪዎችሽ በሙሉ አንዲት ፍላጻ ሳይወረውሩ በሽሽት ላይ እንዳሉ ተማረኩ። ስለ ሞቱት ሕዝቦቼ በመረረ ሁኔታ አለቅስላቸው ዘንድ ተዉኝ፤ አታጽናኑኝ። ይህ በራእይ ሸለቆ የጭንቅ፥ የመረገጥ፥ የሽብር ጊዜ ነው፤ ይህ ሁሉ በእኛ ላይ እንዲፈጸም የፈቀደው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የከተማችን ቅጽሮች ፈራርሰው ወድቀዋል፤ ርዳታ ለማግኘት የሚደረገውም ጩኸት እስከ ተራራዎች በማስተጋባት ላይ ነው። የዔላም አገር ወታደሮች በሠረገላና በፈረስ ተቀምጠው ቀስትና ፍላጻ አንግበው መጡ፤ የቂር ወታደሮች ጋሻቸውን አዘጋጅተዋል። የይሁዳ ለምለም ሸለቆዎች በሠረገሎች የተሞሉ ሆነዋል። ፈረሰኞች በኢየሩሳሌም ቅጽር በር ፊት ለፊት ቆመዋል። የይሁዳ ምሽጎች ሁሉ ተደምስሰዋል፤ በዚያን ጊዜ በጦር ግምጃ ቤት ውስጥ የተከማቸውን የጦር መሣሪያ ወሰዳችሁ። የዳዊት ከተማ ብዙ ፍርስራሾች መብዛታቸውን ተመልክታችኋል፤ ከታችኛውም ኩሬ ውሃ አጠራቀማችሁ። በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ሁሉ እየተዘዋወራችሁ ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለማደስ አንዳንዶቹን ቤቶች አፈረሳችሁ። ከጥንቱ ኲሬ የሚወርደውን ውሃ ለመመለስ በከተማይቱ ውስጥ ግድብ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በመጀመሪያ ዐቅዶ ያደረገው እግዚአብሔር መሆኑ ትዝ አላላችሁም። በዚያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ፥ ማቅም ለብሳችሁ እንድታዝኑና እንድታለቅሱ ጠርቶአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጥሪውን በመቀበል ፈንታ በዓል አደረጋችሁ፤ የምትበሉትንም በግና በሬ ዐረዳችሁ፤ ወይን ጠጅም ጠጥታችሁ “ነገ እንሞታለን ዛሬ እንብላ እንጠጣ!” አላችሁ። የሠራዊት አምላክ እንዲህ ብሎ ነግሮኛል፦ “በሕይወት እስካሉ ድረስ ይህ ክፉ በደል አይሰረይላቸውም፤ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
ትንቢተ ኢሳይያስ 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 22:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች