ኢሳይያስ 22:1-14

ኢሳይያስ 22:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ስለ ጽዮን ሸለቆ የተ​ነ​ገረ ቃል። እና​ንተ ሁላ​ችሁ፥ ዛሬ ወደ ሰገ​ነት በከ​ንቱ መው​ጣ​ታ​ችሁ ምን ሆና​ች​ኋል? ጩኸ​ትና ፍጅ​ትም የተ​ሞ​ላ​ብሽ ከተማ ሆይ፥ ቍስ​ለ​ኞ​ችሽ በሰ​ይፍ የቈ​ሰሉ አይ​ደ​ሉም፤ በአ​ንቺ ውስጥ የተ​ገ​ደ​ሉ​ትም በሰ​ልፍ የተ​ገ​ደሉ አይ​ደ​ሉም። ነገር ግን አለ​ቆ​ችሽ ሁሉ በአ​ን​ድ​ነት ሸሹ፤ የተ​ማ​ረ​ኩ​ት​ንም በእ​ግር ብረት አሠ​ቃ​ዩ​አ​ቸው፤ ኀይ​ለ​ኞ​ች​ሽም ርቀው ሸሹ። ስለ​ዚህ፥ “ተዉኝ እኔ መራራ ልቅሶ አለ​ቅ​ሳ​ለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋ​ትም ታጽ​ና​ኑኝ ዘንድ አት​ድ​ከሙ፥” አልሁ። ከሠ​ራ​ዊት ጌታ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የሁ​ከ​ትና የጥ​ፋት፥ የመ​ረ​ገ​ጥና የስ​ብ​ራ​ትም ቀን በጽ​ዮን ሸለቆ ውስጥ ሆኖ​አል። ታና​ሹና ታላ​ቁም ሸሽ​ተው በተ​ራራ ላይ ይቅ​በ​ዘ​በ​ዛሉ። የኤ​ላ​ምም ሰዎች አፎ​ታ​ቸ​ውን ተሸ​ከሙ፤ በፈ​ረስ የተ​ቀ​መ​ጡና አር​በ​ኞች ሰዎች፥ የአ​ር​በ​ኞ​ችም ሠራ​ዊት ነበሩ። መል​ካ​ሞ​ቹን ሸለ​ቆ​ች​ሽ​ንም ሰረ​ገ​ሎች ሞሉ​ባ​ቸው፤ ፈረ​ሰ​ኞ​ችም መቆ​ሚ​ያ​ቸ​ውን በበ​ሮ​ችሽ ላይ አደ​ረጉ። የይ​ሁ​ዳ​ንም በሮች ይከ​ፍ​ታሉ፤ በዚ​ያም ቀን የከ​ተ​ማ​ይ​ቱን መኳ​ን​ንት ቤቶች ይበ​ረ​ብ​ራሉ። የዳ​ዊት ቤት መዛ​ግ​ብ​ት​ንም ይከ​ፍ​ታሉ። የዳ​ዊ​ትም ከተማ ፍራ​ሾች እን​ደ​በዙ አይ​ታ​ች​ኋል፤ የታ​ች​ኛ​ው​ንም ኵሬ ውኃ በከ​ተማ አከ​ማ​ች​ታ​ች​ኋል፤ የኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ም​ንም ቤቶች ቈጠ​ራ​ችሁ፤ ቅጥ​ሩ​ንም ለማ​ጽ​ናት ቤቶ​ችን አፈ​ረ​ሳ​ችሁ። በአ​ሮ​ጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁ​ለቱ ቅጥር መካ​ከል መከ​ማቻ ሠራ​ችሁ፤ ይህን ያደ​ረ​ገ​ውን ግን አል​ተ​መ​ለ​ከ​ታ​ች​ሁም፤ ቀድሞ የሠ​ራ​ው​ንም አላ​ያ​ች​ሁም። በዚ​ያም ቀን የሠ​ራ​ዊት ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልቅ​ሶ​ንና ዋይ​ታን፥ ራስን መን​ጨ​ት​ንና ማቅን መል​በ​ስን ጠራ። እነ​ሆም፥ በዓ​ልን፥ ደስ​ታ​ንና ሐሴ​ትን አደ​ረ​ጋ​ችሁ፤ በሬ​ዎ​ች​ንና በጎ​ች​ንም አረ​ዳ​ችሁ፤ “ነገ እን​ሞ​ታ​ለን፤ እን​ብላ፤ እን​ጠ​ጣም፤” እያ​ላ​ችሁ ሥጋን በላ​ችሁ፤ ወይ​ን​ንም ጠጣ​ችሁ። ይህም ነገር በሠ​ራ​ዊት ጌታ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጆሮ ተሰማ፥ “እስ​ክ​ት​ሞቱ ድረስ ይህ በደል በእ​ው​ነት አይ​ሰ​ረ​ይ​ላ​ች​ሁም” ይላል የሠ​ራ​ዊት ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር።

ኢሳይያስ 22:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ንግር፤ እስኪ ምን ቢጨንቃችሁ ነው ሁላችሁም ሰገነት ላይ የወጣችሁት? አንቺ ጫጫታ የሞላብሽ ከተማ፤ የውካታና የፈንጠዝያ ከተማ ሆይ፤ የተገደሉብሽ በሰይፍ የተሠዉ አይደሉም፤ በጦርነትም አልሞቱም። መሪዎችሽ በሙሉ በአንድ ላይ ሸሽተዋል፤ ቀስት እንኳ ሳያነሡ ተማርከዋል፤ ጠላት ገና በሩቅ ሳለ የሸሻችሁ ሁሉ፣ ተይዛችሁ በአንድነት ታስራችኋል። ስለዚህ፣ “ከእኔ ራቁ፤ አምርሬ ላልቅስበት፣ ስለ ሕዝቤ ጥፋት፣ ልታጽናኑኝ አትሞክሩ” አልሁ። ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በራእይ ሸለቆ፣ የመጯጯኺያ፣ የመረገጥና የሽብር፣ ቅጥሮችን የማፈራረስ፣ ወደ ተራሮችም የሚጮኽበት ቀን አለው። ኤላም የፍላጻ ሰገባ፣ ፈረሷንና ሠረገላዋን አዘጋጀች፤ ቂርም ጋሻዋን አነገበች። መልካሞቹ ሸለቆዎችሽ በሠረገሎች ተሞልተዋል፤ ፈረሰኞችም በከተማዪቱ በሮች ላይ ቆመዋል። የይሁዳን መከላከያዎች ገልጧል። በዚያ ቀን በዱር ግምጃ ቤት የነበረውን፣ የጦር መሣሪያ ተመለከትህ፤ የዳዊት ከተማ ብዙ ፍርስራሾች እንዳሉበት አያችሁ፤ በታችኛውም ኵሬ፣ ውሃ አጠራቀማችሁ። በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለመጠገንም ቤቶቹን አፈረሳችሁ። ለጥንቱ ኵሬ ውሃ የሚሆን፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል ውሃ ማጠራቀሚያ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገውን አልተመለከታችሁም፤ ቀድሞ ዐቅዶ የሠራውንም አላስታወሳችሁም። በዚያ ቀን ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንድታለቅሱና በዋይታ እንድትጮኹ፣ ጠጕራችሁን እንድትነጩ ማቅም እንድትለብሱ ጠራችሁ። ነገር ግን እነሆ፤ ደስታና ሐሤት፣ ፍሪዳ መጣልና ሙክት ማረድ፣ ሥጋ መብላትና የወይን ጠጅ መጠጣት አለ! “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፤ እንጠጣ!” አላችሁ። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ገለጠልኝ፤ እንዲህም ሲል በጆሮዬ ሰማሁ፤ “ይህ ኀጢአት እስከምትሞቱበት ቀን ድረስ አይሰረይላችሁም” ይላል ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 22:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ሸክም። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታችሁ ምን ሆናችኋል? ጩኸትና ፍጅት የተሞላብሽ ከተማ፥ ደስታ ያለሽ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉም፥ በሰልፍም የሞቱ አይደሉም። አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፥ ከሩቅ ሸሽተው ከአንቺ ዘንድ የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ። ስለዚህ፦ ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፥ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፥ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ፥ አልሁ። ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የድንጋጤና የመረገጥ የድብልቅልቅም ቀን፥ የቅጥርን መፍረስ ወደ ተራራ መጮኽ በራእይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል። ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን ገለጠ። መልካሞቹንም ሸለቆችሽን ሰረገሎች ሞሉባቸው፥ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበር ላይ አደረጉ። የይሁዳንም መጋረጃ ገለጠ፥ በዚያም ቀን በዱር ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፥ የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደበዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ አከማችታችኋል፥ የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ፥ ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ። በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፥ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ የሠራውንም አላያችሁም። በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ። እነሆም፥ ሐሤትና ደስታ በሬንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፥ እናንተ፦ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል። ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ፦ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 22:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“የራእይ ሸለቆ” ተብሎ ስለሚጠራው ቦታ የተነገረ ቃል ይህ ነው፤ በየቤታችሁ ሰገነት ላይ ሆናችሁ በዓል የምታከብሩት በምን ምክንያት ነው? በሁካታና በጩኸት የተሞላሽ አንቺ ከተማ ሆይ! ሰክረው በመንገዶችሽ ላይ የወደቁት ሰዎች በሰይፍ የተገደሉ ወይም በጦርነት የሞቱ አይደሉም። መሪዎችሽ በሙሉ አንዲት ፍላጻ ሳይወረውሩ በሽሽት ላይ እንዳሉ ተማረኩ። ስለ ሞቱት ሕዝቦቼ በመረረ ሁኔታ አለቅስላቸው ዘንድ ተዉኝ፤ አታጽናኑኝ። ይህ በራእይ ሸለቆ የጭንቅ፥ የመረገጥ፥ የሽብር ጊዜ ነው፤ ይህ ሁሉ በእኛ ላይ እንዲፈጸም የፈቀደው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የከተማችን ቅጽሮች ፈራርሰው ወድቀዋል፤ ርዳታ ለማግኘት የሚደረገውም ጩኸት እስከ ተራራዎች በማስተጋባት ላይ ነው። የዔላም አገር ወታደሮች በሠረገላና በፈረስ ተቀምጠው ቀስትና ፍላጻ አንግበው መጡ፤ የቂር ወታደሮች ጋሻቸውን አዘጋጅተዋል። የይሁዳ ለምለም ሸለቆዎች በሠረገሎች የተሞሉ ሆነዋል። ፈረሰኞች በኢየሩሳሌም ቅጽር በር ፊት ለፊት ቆመዋል። የይሁዳ ምሽጎች ሁሉ ተደምስሰዋል፤ በዚያን ጊዜ በጦር ግምጃ ቤት ውስጥ የተከማቸውን የጦር መሣሪያ ወሰዳችሁ። የዳዊት ከተማ ብዙ ፍርስራሾች መብዛታቸውን ተመልክታችኋል፤ ከታችኛውም ኩሬ ውሃ አጠራቀማችሁ። በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ሁሉ እየተዘዋወራችሁ ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለማደስ አንዳንዶቹን ቤቶች አፈረሳችሁ። ከጥንቱ ኲሬ የሚወርደውን ውሃ ለመመለስ በከተማይቱ ውስጥ ግድብ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በመጀመሪያ ዐቅዶ ያደረገው እግዚአብሔር መሆኑ ትዝ አላላችሁም። በዚያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ፥ ማቅም ለብሳችሁ እንድታዝኑና እንድታለቅሱ ጠርቶአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጥሪውን በመቀበል ፈንታ በዓል አደረጋችሁ፤ የምትበሉትንም በግና በሬ ዐረዳችሁ፤ ወይን ጠጅም ጠጥታችሁ “ነገ እንሞታለን ዛሬ እንብላ እንጠጣ!” አላችሁ። የሠራዊት አምላክ እንዲህ ብሎ ነግሮኛል፦ “በሕይወት እስካሉ ድረስ ይህ ክፉ በደል አይሰረይላቸውም፤ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

ኢሳይያስ 22:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ራእይ። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታችሁ ምን ማለት ነው? አንቺ ጩኸትና ፍጅት የሞላብሽ ከተማ፥ የፈንጠዚያ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉምን፥ በሰልፍስ የሞቱ አይደሉም? አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፤ እርቀው ቢሸሹም አንቺ ጋር የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ። ስለዚህ፦ “ከእኔ እራቁ፤ መራራ ልቅሶ ላልቅስበት፤ ስለ ሕዝቤ ጥፋት ልታጽናኑኝ አትድከሙ” አልኩ። ከሠራዊት ከጌታ በራእይ ሸለቆ ውስጥ የድንጋጤና የመረገጥ፥ ግራ የመጋባት፥ የቅጥር መፍረስና ወደ ተራራ ለእርዳታ የሚጮኽበት ቀን ሆኖአል። ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን አነገበ። ምርጦቹም ሸለቆችሽ ሠረገሎች ሞሉባቸው፤ ፈረሰኞችም በሮች ላይ ቆመዋል። የይሁዳንም መጋረጃ ገልጧል። በዚያም ቀን በዱር ግምጃ ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፤ የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደበዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኩሬ ውኃ አጠራቅማችኋል። የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ፥ ቅጥሩንም ለመጠገን ቤቶችን አፈረሳችሁ። በአሮጌው ኩሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ አቅዶ የሠራውንም አላስታወሳችሁም። በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ፥ ጠጉራችሁን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራችሁ። ነገር ግን እናንተ፦ “ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣም” በማለት እነሆም፥ በሐሤትና በደስታ በሬንና በጉንም ስታርዱ፥ ሥጋንም ስትበሉ፥ የወይን ጠጅንም ስትጠጡ ነበር። ይህም ነገር የሠራዊት ጌታ ይህንን በጆሮዬ ነገረኝ፤ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።