ኢሳይያስ 22:1-14

ኢሳይያስ 22:1-14 NASV

ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ንግር፤ እስኪ ምን ቢጨንቃችሁ ነው ሁላችሁም ሰገነት ላይ የወጣችሁት? አንቺ ጫጫታ የሞላብሽ ከተማ፤ የውካታና የፈንጠዝያ ከተማ ሆይ፤ የተገደሉብሽ በሰይፍ የተሠዉ አይደሉም፤ በጦርነትም አልሞቱም። መሪዎችሽ በሙሉ በአንድ ላይ ሸሽተዋል፤ ቀስት እንኳ ሳያነሡ ተማርከዋል፤ ጠላት ገና በሩቅ ሳለ የሸሻችሁ ሁሉ፣ ተይዛችሁ በአንድነት ታስራችኋል። ስለዚህ፣ “ከእኔ ራቁ፤ አምርሬ ላልቅስበት፣ ስለ ሕዝቤ ጥፋት፣ ልታጽናኑኝ አትሞክሩ” አልሁ። ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በራእይ ሸለቆ፣ የመጯጯኺያ፣ የመረገጥና የሽብር፣ ቅጥሮችን የማፈራረስ፣ ወደ ተራሮችም የሚጮኽበት ቀን አለው። ኤላም የፍላጻ ሰገባ፣ ፈረሷንና ሠረገላዋን አዘጋጀች፤ ቂርም ጋሻዋን አነገበች። መልካሞቹ ሸለቆዎችሽ በሠረገሎች ተሞልተዋል፤ ፈረሰኞችም በከተማዪቱ በሮች ላይ ቆመዋል። የይሁዳን መከላከያዎች ገልጧል። በዚያ ቀን በዱር ግምጃ ቤት የነበረውን፣ የጦር መሣሪያ ተመለከትህ፤ የዳዊት ከተማ ብዙ ፍርስራሾች እንዳሉበት አያችሁ፤ በታችኛውም ኵሬ፣ ውሃ አጠራቀማችሁ። በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለመጠገንም ቤቶቹን አፈረሳችሁ። ለጥንቱ ኵሬ ውሃ የሚሆን፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል ውሃ ማጠራቀሚያ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገውን አልተመለከታችሁም፤ ቀድሞ ዐቅዶ የሠራውንም አላስታወሳችሁም። በዚያ ቀን ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንድታለቅሱና በዋይታ እንድትጮኹ፣ ጠጕራችሁን እንድትነጩ ማቅም እንድትለብሱ ጠራችሁ። ነገር ግን እነሆ፤ ደስታና ሐሤት፣ ፍሪዳ መጣልና ሙክት ማረድ፣ ሥጋ መብላትና የወይን ጠጅ መጠጣት አለ! “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፤ እንጠጣ!” አላችሁ። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ገለጠልኝ፤ እንዲህም ሲል በጆሮዬ ሰማሁ፤ “ይህ ኀጢአት እስከምትሞቱበት ቀን ድረስ አይሰረይላችሁም” ይላል ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።