ትንቢተ ኢሳይያስ 22:1-14

ትንቢተ ኢሳይያስ 22:1-14 አማ54

ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ሸክም። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታችሁ ምን ሆናችኋል? ጩኸትና ፍጅት የተሞላብሽ ከተማ፥ ደስታ ያለሽ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉም፥ በሰልፍም የሞቱ አይደሉም። አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፥ ከሩቅ ሸሽተው ከአንቺ ዘንድ የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ። ስለዚህ፦ ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፥ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፥ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ፥ አልሁ። ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የድንጋጤና የመረገጥ የድብልቅልቅም ቀን፥ የቅጥርን መፍረስ ወደ ተራራ መጮኽ በራእይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል። ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን ገለጠ። መልካሞቹንም ሸለቆችሽን ሰረገሎች ሞሉባቸው፥ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበር ላይ አደረጉ። የይሁዳንም መጋረጃ ገለጠ፥ በዚያም ቀን በዱር ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፥ የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደበዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ አከማችታችኋል፥ የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ፥ ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ። በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፥ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ የሠራውንም አላያችሁም። በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ። እነሆም፥ ሐሤትና ደስታ በሬንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፥ እናንተ፦ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል። ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ፦ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።