ያዕቆብ ጓዙን ሁሉ ይዞ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም በደረሰ ጊዜ ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔር፥ ሌሊት በራእይ ተገለጠለትና “ያዕቆብ! ያዕቆብ!” ብሎ ጠራው። እርሱም “አቤት ጌታ ሆይ፥ እነሆ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ እግዚአብሔር ነኝ፤ ወደ ግብጽ ለመሄድ አትፍራ፤ እኔ ዘርህን በግብጽ አገር ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ፤ እኔ ወደ ግብጽ አብሬህ እሄዳለሁ፤ ወደዚህ ምድርም ትውልድህን መልሼ አመጣለሁ፤ በምትሞትበትም ጊዜ ዮሴፍ በአጠገብህ ይገኛል።” ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ግብጽ ጒዞ ጀመረ፤ ልጆቹም አባታቸውን ያዕቆብን፥ ሕፃናት ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን የግብጽ ንጉሥ በላካቸው ሠረገሎች አሳፍረው፥ ከብቶቻቸውንና በከነዓን ያፈሩትን ሀብት ሁሉ ይዘው ወደ ግብጽ ሄዱ፤ በዚህ ዐይነት ያዕቆብ ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ግብጽ ሄደ፤ አብረው የሄዱትም ወንዶች ልጆቹ፥ ሴቶች ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ናቸው። ከእስራኤል ጋር ወደ ግብጽ የወረዱት የእስራኤላውያን ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ የያዕቆብ የበኲር ልጅ ሮቤል፥ የሮቤል ልጆች፦ ሔኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ ናቸው። የስምዖን ልጆች፦ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሻኡል ናቸው። የሌዊ ልጆች፦ ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ ናቸው። የይሁዳ ልጆች፦ ዔር፥ ኦናን፥ ሴላ፥ ፋሬስና ዛራሕ ናቸው፤ ዔርና ኦናን ግን በከነዓን ምድር ሞተዋል። የፋሬስ ልጆች ሔጽሮንና ሐሙል ናቸው። የይሳኮር ልጆች፦ ቶላዕ፥ ፉዋ፥ ያሹብና ሺምሮን ናቸው። የዛብሎን ልጆች፦ ሴሬድ፥ ኤሎንና ያሕለኤል ናቸው። እነዚህ ወንዶች ልጆችና ሴቷም ልጅ ዲና በመስጴጦምያ ሳሉ ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ናቸው። ያዕቆብ ከልያ ያፈራቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ሠላሳ ሦስት ናቸው። የጋድ ልጆች፦ ጸፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤጽቦን፥ ዔሪ፥ አሮድና አርኤሊ ናቸው። የአሴር ልጆች፦ ይምና፥ ይሽዋ፥ ይሽዊና በሪዓ ናቸው። እኅታቸው ሤራሕ ትባላለች። የበሪዓ ልጆች ደግሞ ሔቤርና ማልኪኤል ናቸው። እነዚህ ዐሥራ ስድስቱ ላባ ለልጁ ለልያ በሞግዚትነት ከሰጣት ከዚልፋ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ናቸው፤ እነርሱም ዮሴፍ በግብጽ ምድር ከኦን ከተማ ካህን ከጶጢፌራ ሴት ልጅ ከአስናት የወለዳቸው ናቸው። የብንያም ልጆች፦ ቤላዕ፥ ቤኬር፥ አሽቤል፥ ጌራ፥ ናዕማን፥ ኤሒ፥ ሮሽ፥ ሙፊም፥ ሑፊምና አረድ ናቸው። እነዚህ ዐሥራ አራቱ ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። የዳን ልጅ ሑሺም ነው። የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጼርና ሺሌም ናቸው። እነዚህ ሰባቱ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የሄዱት የያዕቆብ ቤተሰቦች ሥልሳ ስድስት ናቸው፤ ይህም የልጆቹን ሚስቶች ቊጥር ሳይጨምር ነው። ለዮሴፍ በግብጽ ከተወለዱት ከሁለቱ ወንዶች ልጆች ጋር፥ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ቊጥር በአጠቃላይ ሰባ ነበር።
ኦሪት ዘፍጥረት 46 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 46:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች