እስራኤልም ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም ሲደርስ፣ ለአባቱ ለይሥሐቅ አምላክ መሥዋዕት ሠዋ። እግዚአብሔርም ሌሊት በራእይ ለእስራኤል ተገልጦ “ያዕቆብ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የአባትህ አምላክ ነኝ፤ ወደ ግብጽ ለመውረድ አትፍራ፤ በዚያ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና፤ ዐብሬህ ወደ ግብጽ እወርዳለሁ፤ ከዚያም መልሼ አወጣሃለሁ፤ የዮሴፍ የራሱ እጆችም ዐይኖችህን ይገጥሟቸዋል።” ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን ለያዕቆብ በላካቸው ሠረገላዎች ላይ አወጧቸው። ከብቶቻቸውንና በከነዓን ምድር ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው፣ ያዕቆብና ዘሮቹ በሙሉ ወደ ግብጽ ወረዱ። ወደ ግብጽም የወረደው፣ ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን፣ ማለትም ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ነው። ወደ ግብጽ የወረዱት የእስራኤል ልጆች፣ ያዕቆብና ዘሮቹ እነዚህ ናቸው፦ የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል። የሮቤል ልጆች፦ ሄኖኅ፣ ፈሉስ፣ አስሮን እና ከርሚ ናቸው። የስምዖን ልጆች፦ ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሳኡል ናቸው። የሌዊ ልጆች፦ ጌርሶን፣ ቀዓት እና ሜራሪ ናቸው። የይሁዳ ልጆች፦ ዔር፣ አውናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ናቸው። ነገር ግን ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ። የፋሬስ ልጆች፦ ኤስሮምና ሐሙል ናቸው። የይሳኮር ልጆች፦ ቶላ፣ ፉዋ፣ ዮብና ሺምሮን ናቸው፤ የዛብሎን ልጆች፦ ሴሬድ፣ ኤሎንና ያሕልኤል ናቸው፤ እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ፣ ልያ የወለደችለት ናቸው። ሴቷን ዲናን ጨምሮ፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ቍጥር ሠላሳ ሦስት ነው። የጋድ ልጆች፦ ጽፎን፣ ሐጊ፣ ሹኒ፣ ኤስቦን፣ ዔሪ፣ አሮዲና አርኤሊ ናቸው፤ የአሴር ልጆች፦ ዪምና፣ የሱዋ፣ የሱዊና በሪዓ ናቸው፤ እኅታቸውም ሤራሕ ናት፤ የበሪዓ ልጆች፦ ሔቤርና መልኪኤል ናቸው፤ እነዚህ ዐሥራ ስድስት ልጆች ሁሉ፣ ላባ ለልጁ ለልያ ከሰጣት ከዘለፋ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍና ብንያም ናቸው፤ በግብጽም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት፣ ምናሴንና ኤፍሬምን ለዮሴፍ ወለደችለት። የብንያም ልጆች፦ ቤላ፣ ቤኬር፣ አስቤል፣ ጌራ፣ ናዕማን፣ አኪ፣ ሮስ፣ ማንፌን ሑፊምና አርድ ናቸው። እነዚህ ዐሥራ አራቱ፣ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። የዳን ልጅ፦ ሑሺም ነው፤ የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፣ ጉኒ፣ ዬጽርና ሺሌም ናቸው። እነዚህ ሰባቱ ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። ከያዕቆብ ጋራ ወደ ግብጽ የሄዱት የገዛ ዘሮቹ ብዛት ስድሳ ስድስት ሲሆን ይህ ቍጥር ግን የልጆቹን ሚስቶች አይጨምርም። ዮሴፍ በግብጽ የወለዳቸውን ሁለት ልጆች ጨምሮ፣ ወደ ግብጽ የወረደው የያዕቆብ ቤተ ሰብ ቍጥር ሰባ ነበር።
ዘፍጥረት 46 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 46
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 46:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች