ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ ልቡን በማደንደን ሕዝቡን አለቅም ብሎአል፤ ስለዚህ ጠዋት በማለዳ ወደ ንጉሡ ሂድ፤ ወደ ዐባይ ወንዝ ሲወርድ ወደ እባብነት የተለወጠችውን በትር ይዘህ በወንዙ ዳር ቆመህ ጠብቀው። እንዲህም በለው፥ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር በበረሓ ያገለግሉት ዘንድ ሕዝቡን እንድትለቅ እንድነግርህ ወደ አንተ ልኮኛል፤ አንተ ግን እስከ ዛሬ እምቢ ብለሃል። አሁን ግን በሚያደርገው ነገር የእግዚአብሔርን ማንነት በግድ ታውቃለህ፤ እነሆ፥ እኔ በዚህ በትር የአባይን ወንዝ ውሃ እመታለሁ፤ ውሃውም ወደ ደም ይለወጣል። በውስጡ ያሉ ዓሣዎች ሁሉ ይሞታሉ፤ የዐባይ ውሃ በጣም ከመሽተቱ የተነሣ ግብጻውያን ከዚህ ወንዝ ውሃ ቀድተው መጠጣት አይችሉም።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮን በትሩን ወስዶ በግብጽ ምድር በሚገኙት ወንዞች፥ ቦዮችና ኲሬዎች ሁሉ ላይ እንዲዘረጋ ንገረው፤ በዚያን ጊዜ ውሃው ሁሉ ተለውጦ ደም ይሆናል፤ ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩት የውሃ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀር በግብጽ ምድር የሚገኘው ውሃ ሁሉ ደም ይሆናል።” ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አሮንም በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የወንዙን ውሃ መታው። የወንዙም ውሃ ተለውጦ ደም ሆነ፤ በወንዝ ውስጥ ያሉት ዓሣዎች ሁሉ ሞቱ፤ የዐባይ ወንዝ ውሃ ስለ ገማ ግብጻውያን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ደም የሌለበት ስፍራ አልነበረም። ከዚህ በኋላ የንጉሡ አስማተኞች በአስማታቸው እንደዚሁ አደረጉ፤ ንጉሡም ልቡን በማደንደን ጸና፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም ንጉሡ ሙሴንና አሮንን ማዳመጥ እምቢ አለ። የሆነውን ነገር ሁሉ ከቁም ነገር ሳይቈጥረው ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመልሶ ሄደ። ግብጻውያን ከዐባይ ወንዝ ውሃ መጠጣት ስላልቻሉ የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ከዐባይ ወንዝ ዳር ጒድጓድ ቈፈሩ። እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን አለፈ።
ኦሪት ዘጸአት 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 7:14-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
YouVersion የእርስዎን ተሞክሮ ግላዊ ለማድረግ ኩኪዎችን ይጠቀማል። የእኛን ድረ ገጽ በመጠቀም፣ በግለሰብነት መመሪያችን ላይ እንደተገለጸው የእኛን የኩኪዎች አጠቃቀም ተቀብለዋል
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች