ዘፀአት 7:14-25

ዘፀአት 7:14-25 NASV

ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም። ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ። ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ ዕሺ አላልህም። እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ! በዚህች በእጄ በያዝኋት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ፤ ወደ ደምም ይለወጣል። በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብጻውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።” ’ ” እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብጽ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኵሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከዕንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብጽ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።” ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ፤ ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ። በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብጻውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ሁሉ ደም ነበረ። የግብጽ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም። ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህን ከቁም ነገር አልቈጠረውም። ግብጻውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጕድጓድ ቈፈሩ። እግዚአብሔር አባይን ከመታ ሰባት ቀን ሞላ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}