ኦሪት ዘጸአት 7
7
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አደርግሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን እንደ ነቢይ ሆኖ ስለ አንተ ይናገራል፤ 2እኔ የማዝህን ሁሉ ለአሮን ንገረው፤ እርሱም ከአገሩ እንዲወጡ እስራኤላውያንን ይለቅ ዘንድ ለንጉሡ ይነግረዋል፤ 3ነገር ግን እኔ የንጉሡን ልብ አደነድናለሁ፤ ከዚህም የተነሣ እኔ የቱንም ያኽል ምልክቶችንና ተአምራትን በግብጽ ምድር ባደርግ፥ #ሐ.ሥ. 7፥36። 4እናንተን አይሰማችሁም፤ ከዚያን በኋላ በግብጽ ላይ በታላቅ ፍርድ ብርቱ ቅጣት በማምጣት ሠራዊቴን፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከምድረ ግብጽ አስወጣቸዋለሁ። 5በዚህ ዐይነት የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አንሥቼ እስራኤላውያንን ከአገራቸው በማወጣበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” 6ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ ፈጸሙ። 7ከንጉሡም ጋር በተነጋገሩበት በዚያ ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ዕድሜ ሲኖረው፥ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበር።
የአሮን በትር
8እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 9“ፈርዖን ‘እስቲ ተአምራት በማድረግ ማንነታችሁን ግለጡልኝ’ ቢላችሁ ለአሮን ንገረውና በትሩን ወስዶ በንጉሡ ፊት ይጣለው፤ በዚያን ጊዜ በትሩ ተለውጦ እባብ ይሆናል።” 10ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት በጣለው ጊዜ ተለውጦ እባብ ሆነ። 11ከዚህም በኋላ ፈርዖን ጠቢባኑንና አስማተኞቹን ጠራ፤ እነርሱም በአስማታቸው እንደዚሁ አደረጉ። 12በትሮቻቸውን ወደ መሬት በጣሉአቸው ጊዜ ተለውጠው እባቦች ሆኑ፤ ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ሁሉ ዋጠች። 13ይህም ሁሉ ከሆነ በኋላ ንጉሡ ልቡን በማደንደን ጸና፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን ሊሰማቸው አልፈለገም።
ግብጽ በተአምራዊ መቅሠፍት ተመታች
ሀ. ውሃው ወደ ደም ስለ መለወጡ
14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ ልቡን በማደንደን ሕዝቡን አለቅም ብሎአል፤ 15ስለዚህ ጠዋት በማለዳ ወደ ንጉሡ ሂድ፤ ወደ ዐባይ ወንዝ ሲወርድ ወደ እባብነት የተለወጠችውን በትር ይዘህ በወንዙ ዳር ቆመህ ጠብቀው። 16እንዲህም በለው፥ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር በበረሓ ያገለግሉት ዘንድ ሕዝቡን እንድትለቅ እንድነግርህ ወደ አንተ ልኮኛል፤ አንተ ግን እስከ ዛሬ እምቢ ብለሃል። 17አሁን ግን በሚያደርገው ነገር የእግዚአብሔርን ማንነት በግድ ታውቃለህ፤ እነሆ፥ እኔ በዚህ በትር የአባይን ወንዝ ውሃ እመታለሁ፤ ውሃውም ወደ ደም ይለወጣል። #ራዕ. 16፥4። 18በውስጡ ያሉ ዓሣዎች ሁሉ ይሞታሉ፤ የዐባይ ውሃ በጣም ከመሽተቱ የተነሣ ግብጻውያን ከዚህ ወንዝ ውሃ ቀድተው መጠጣት አይችሉም።’ ”
19እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አሮን በትሩን ወስዶ በግብጽ ምድር በሚገኙት ወንዞች፥ ቦዮችና ኲሬዎች ሁሉ ላይ እንዲዘረጋ ንገረው፤ በዚያን ጊዜ ውሃው ሁሉ ተለውጦ ደም ይሆናል፤ ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩት የውሃ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀር በግብጽ ምድር የሚገኘው ውሃ ሁሉ ደም ይሆናል።” #ሉቃ. 11፥20።
20ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አሮንም በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የወንዙን ውሃ መታው። የወንዙም ውሃ ተለውጦ ደም ሆነ፤ 21በወንዝ ውስጥ ያሉት ዓሣዎች ሁሉ ሞቱ፤ የዐባይ ወንዝ ውሃ ስለ ገማ ግብጻውያን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ደም የሌለበት ስፍራ አልነበረም። 22ከዚህ በኋላ የንጉሡ አስማተኞች በአስማታቸው እንደዚሁ አደረጉ፤ ንጉሡም ልቡን በማደንደን ጸና፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም ንጉሡ ሙሴንና አሮንን ማዳመጥ እምቢ አለ። 23የሆነውን ነገር ሁሉ ከቁም ነገር ሳይቈጥረው ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመልሶ ሄደ። 24ግብጻውያን ከዐባይ ወንዝ ውሃ መጠጣት ስላልቻሉ የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ከዐባይ ወንዝ ዳር ጒድጓድ ቈፈሩ።
25እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን አለፈ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997