ኦሪት ዘጸአት 4:1-31

ኦሪት ዘጸአት 4:1-31 አማ05

ሙሴም እግዚአብሔርን “እስራኤላውያን ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ብለው ባያምኑኝና ቃሌን ባይሰሙ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” አለው። እርሱም “በትር ነው” አለ። እግዚአብሔርም “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ ሙሴም ወደ መሬት በጣለው ጊዜ በትሩ ተለውጦ እባብ ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። እግዚአብሔር ግን ሙሴን “እጅህን ዘርጋና ጅራቱን ይዘህ አንሣው” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ጅራቱን በመያዝ ባነሣው ጊዜ እንደገና በትር ሆነ። እግዚአብሔርም “የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተገለጥኩልህ ለእስራኤላውያን ማስረጃ ይሆን ዘንድ በዚህ ተጠቀም” አለው። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ብብትህ አስገባው” አለው፤ እርሱም እጁን ወደ ብብቱ አስገባ፤ እጁንም ከብብቱ ባወጣው ጊዜ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። እግዚአብሔርም “እጅህን እንደገና ወደ ብብትህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ወደ ብብቱ አስገባ፤ መልሶም ባወጣው ጊዜ ተመልሶ እነሆ፥ እንደ ሌላው ሰውነቱ ጤናማ ሆነ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ በመጀመሪያው ተአምር ባያምኑና እውነት ነው ብለው ባይቀበሉህ፥ ሁለተኛውን ተአምር ያምናሉ። እነዚህን ሁለት ተአምራት አይተው ባያምኑና ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከዐባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ወስደህ በመሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ ወንዝ የወሰድከውም ውሃ በደረቀ ምድር ላይ ወደ ደም ይለወጣል።” ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ወደዚያ አትላከኝ፤ ቀድሞም ሆነ ወይም አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ የመናገር ችሎታ የለኝም፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ።” ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍን የፈጠረለት ማነው? ድዳ ወይም ደንቆሮ፥ ዐይኑ እንዲያይ ወይም እንዳያይ የሚያደርግስ ማነው? ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ስለዚህ አሁን ሂድ! እኔም ከአንተ ጋር ሆኜ መናገር እንድትችል አደርጋለሁ፤ ምን መናገር እንደሚገባህ እነግርሃለሁ።” ሙሴም “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለው፤ “ሌዋዊ የሆነው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ ተናጋሪ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልብ ደስ ይለዋል። ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገረውንም ቃል ታስረዳዋለህ፤ ሁለታችሁም እንዴት መናገር እንደምትችሉና ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ አስተምራችኋለሁ፤ እርሱ አንተን ወክሎ ይናገራል፤ በአንተም ስም ቃሉን ለሕዝቡ ያስተላልፋል፤ አንተም ለእርሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ። ተአምራት የምታሳይበትንም ይህን በትር ይዘህ ሂድ።” ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ የትሮ ተመልሶ ሄደና “በግብጽ ወደሚኖሩት ወገኖቼ ተመልሼ ሄጄ በሕይወት መኖራቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። የትሮም ፈቅዶ “በሰላም ሂድ” አለው። ሙሴ ገና በምድያም ሳለ እግዚአብሔር “ሊገድሉህ የሚፈልጉት ሁሉ ስለ ሞቱ ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ” አለው። ስለዚህም ሙሴ ሚስቱንና ወንዶች ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብጽ መጓዝ ጀመረ፤ ተአምራት የሚገለጥበት የእግዚአብሔርንም በትር በእጁ ይዞ ነበር። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ግብጽ መመለስህ ስለ ሆነ፥ በሰጠሁህ ኀይል የምታደርጋቸውን ተአምራት በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ፤ ሆኖም እኔ የፈርዖንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን በቀላሉ አይለቅም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለፈርዖን የምለውን እንዲህ ብለህ ትነግረዋለህ፤ ‘እስራኤል የበኲር ልጄ ነው፤ እኔም ይህ ልጄ እኔን ያመልክ ዘንድ እንድትለቀው ነገርኩህ፤ አንተ ግን እምቢ አልክ፤ ስለዚህ አሁን የአንተን የበኲር ልጅ እገድላለሁ።’ ” ሙሴ ወደ ግብጽ በመጓዝ ላይ ሳለ ባረፈበት ሰፈር እግዚአብሔር አግኝቶት በሞት ሊቀጣው ፈለገ። ከዚያ በኋላ ሲፖራ ሮጣ ሄዳ ባልጩት አመጣችና የልጅዋን ሸለፈት ገረዘች፤ የሙሴንም እግር በሸለፈቱ ዳስሳ “በእርግጥ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። እግዚአብሔርም ለሙሴ ምሕረት አደረገለት፤ እርስዋም “ከግዝረት ሥርዓት የተነሣ አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። በዚያኑ ጊዜ እግዚአብሔር አሮንን “ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ በረሓው ሂድ” አለው። እርሱም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ሄደ፤ በዚያም ሙሴን አግኝቶ ሳመው። ሙሴም እግዚአብሔር ወደ ግብጽ እንዲመለስ ባዘዘው ጊዜ የነገረውን ቃልና እንዲፈጽማቸው ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን አስረዳው። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ወርደው የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን ሁሉ ገለጠላቸው፤ ሙሴም ተአምራትን ሁሉ በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ መጥቶ እንደ ጐበኛቸውና የደረሰባቸውንም የግፍ ጭቈና ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}