ዘፀአት 4:1-31
ዘፀአት 4:1-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም መለሰ፥ “እነሆ፥ ባያምኑኝ፥ ቃሌንም ባይሰሙ፦ ‘እግዚአብሔርም አልተገለጠልህም’ ቢሉኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም፥ “ይህ በእጅህ ያለው ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፥ “በትር ነው” አለ። “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ እርሱም በመሬት ጣለው፤ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዝ” አለው፤ ሙሴም እጁን ዘርግቶ፥ ጅራቱን ይዞ፥ አነሣው በእጁም በትር ሆነ። እግዚአብሔርም፥ “የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ እንደ ታየህ ያምኑሃል” አለው። ዳግመኛም እግዚአብሔር፥ “እጅህን ወደ ብብትህ አግባ አለው።” እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ “እጅህንም ከብብትህ አውጣ” አለው፤ እጁንም ከብብቱ አወጣ፤ እጁም ለምጽ ሆነች። ዳግመኛም፥ “እጅህን ወደ ብብትህ መልስ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፤ “እጅህን ከብብትህ አውጣ” አለው፤ እጁንም ከብብቱ አወጣ፤ ተመልሳም ገላውን መሰለች። ደግሞም አለው፥ “እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ፥ በፊተኛዪቱም ምልክት ቃልህን ባይሰሙ፥ በሁለተኛዪቱ ምልክት ቃልህን ያምናሉ። እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ፥ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፤ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ ትናንት፥ ከትናንት ወዲያ ባሪያህን ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። እኔ አፌ ኰልታፋ፥ ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ።” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? ዲዳስ፥ ደንቆሮስ፥ የሚያይስ፥ ዕውርስ የሚያደርግ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ” አለው። ሙሴም፥ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መናገር የሚችል የምትልከው ሌላ ሰው ፈልግ” አለው። እግዚአብሔርም በሙሴ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፥ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ እንደሚናገርልህ አውቃለሁ፤ እነሆም፥ እርሱ ሊገናኝህ ይመጣል፤ በአየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ፤ ቃሌንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ አንደበትህንና አንደበቱን አረታለሁ፤ የምታደርጉትንም አለብማችኋለሁ። እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይነጋገራል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ዘንድ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ያዝ።” ሙሴም ሄደ፤ ወደ አማቱ ወደ ዮቶርም ተመለሰ፥ “እስከ ዛሬ በሕይወት እንደ አሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞች እሄዳለሁ” አለው። ዮቶርም ሙሴን፥ “በደኅና ሂድ” አለው። ከብዙ ዘመንም በኋላ የግብፅ ንጉሥ ሞተ። እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም፥ “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፤ በአህዮች ላይም አስቀመጣቸው፤ ወደ ግብፅም ሀገር ተመለሰ፤ ሙሴም ያችን የእግዚአብሔርን በትር በእጁ ይዞ ሄደ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ግብፅ ተመልሰህ ስትሄድ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራቴን ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፤ ሕዝቡንም አይለቅቅም። አንተ ግን ፈርዖንን እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ልትለቅቃቸው ባትፈቅድ፤ እኔ የበኵር ልጅህን እንደምገድል ዕወቅ።” እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በአደረበት ስፍራ የእግዚአብሔር መልአክ ተገናኘው፤ ሊገድለውም ፈለገ። ሚስቱ ሲፓራም ባልጩት ወሰደች፤ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፤ “ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላ ከእግሩ በታች ወደቀች። ከእርሱም ሄደ፤ የዚያ ጊዜ፥ “ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላለችና። እግዚአብሔርም አሮንን አለው፥ “ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው፤” ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፤ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ። ሙሴም እግዚአብሔር የላከውን ቃል ሁሉ፥ የአዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ፤ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፤ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ ደስም አላቸው፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ጐብኝቶአልና፤ ጭንቀታቸውንም አይቶአልና፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሰገዱ።
ዘፀአት 4:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው። እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው። እግዚአብሔርም፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው። ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች። እግዚአብሔርም “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው። እግዚአብሔርም ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። “አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች። እግዚአብሔርም፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ። እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ጌታ ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋራ ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል። ለርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ ረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል። ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።” ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብጽ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው። ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብጽ ሂድ” አለው። ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብጽ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርም በትር በእጁ ይዞ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብጽ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ” ሙሴ በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። ስለዚህም እግዚአብሔር ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። ሙሴም እግዚአብሔር እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኛቸውና መከራቸውን እንዳየ በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።
ዘፀአት 4:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም መለሰ፦ “እነሆ አያምኑኝም፤ ቃሌንም አይሰሙም፤ ‘እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም’ ይሉኛል” አለ። እግዚአብሔርም፦ “ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት?” አለው። እርሱም፦ “በትር ናት፤” አለ። “ወደ መሬት ጣላት፤” አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ሙሴም ከእርሷ ሸሸ። እግዚአብሔርም ሙሴ፥ “የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ፥ እግዚአብሔር እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ እጅህን ዘርግተህ ጅራትዋን ያዝ፤” አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዛት በእጁም ውስጥ በትር ሆነች። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ “እጅህን ወደ ብብትህ አግባ፤” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ ባወጣትም ጊዜ እነሆ፥ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። እርሱም፦ እጅህን ወደ ብብትህ መልስ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፥ ከብብቱም ባወጣት ጊዜ እነሆ ተመልሳ ገላውን መሰለች። ደግሞም አለው፦ “እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ነገር ባይሰሙ፥ የሁለተኛይቱን ምልክት ነገር ያምናሉ። እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፤ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ጌታ ሆይ! እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።” እግዚአብሔርም፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ፤” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ! በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ፤ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፤ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ፈንታ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።” ሙሴም ሄደ፤ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመለሰ፤ “እስከ ዛሬ በሕይወት እንዳሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞቼ ልሂድ፤” አለው። ዮቶርም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም፥ “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ፤” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፤ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፤ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፤ ሕዝቡንም አይለቅቅም። ፈርዖንንም፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ’ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ”’ ትለዋለህ። እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፤ ሊገድለውም ፈለገ። ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፤ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፤ ወደ እግሩም ጣለችው፤ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ፤” አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ ስለ ግርዛቱ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። እግዚአብሔርም አሮንን፦ “ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው፤” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፤ ሳመውም። ሙሴም እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የላከውን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፤ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጎበኘ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ፤ ሰገዱም።
ዘፀአት 4:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴም እግዚአብሔርን “እስራኤላውያን ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ብለው ባያምኑኝና ቃሌን ባይሰሙ ምን እላቸዋለሁ?” አለው። እግዚአብሔርም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” አለው። እርሱም “በትር ነው” አለ። እግዚአብሔርም “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ ሙሴም ወደ መሬት በጣለው ጊዜ በትሩ ተለውጦ እባብ ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። እግዚአብሔር ግን ሙሴን “እጅህን ዘርጋና ጅራቱን ይዘህ አንሣው” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ጅራቱን በመያዝ ባነሣው ጊዜ እንደገና በትር ሆነ። እግዚአብሔርም “የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተገለጥኩልህ ለእስራኤላውያን ማስረጃ ይሆን ዘንድ በዚህ ተጠቀም” አለው። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ብብትህ አስገባው” አለው፤ እርሱም እጁን ወደ ብብቱ አስገባ፤ እጁንም ከብብቱ ባወጣው ጊዜ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። እግዚአብሔርም “እጅህን እንደገና ወደ ብብትህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ወደ ብብቱ አስገባ፤ መልሶም ባወጣው ጊዜ ተመልሶ እነሆ፥ እንደ ሌላው ሰውነቱ ጤናማ ሆነ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ በመጀመሪያው ተአምር ባያምኑና እውነት ነው ብለው ባይቀበሉህ፥ ሁለተኛውን ተአምር ያምናሉ። እነዚህን ሁለት ተአምራት አይተው ባያምኑና ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከዐባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ወስደህ በመሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ ወንዝ የወሰድከውም ውሃ በደረቀ ምድር ላይ ወደ ደም ይለወጣል።” ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ወደዚያ አትላከኝ፤ ቀድሞም ሆነ ወይም አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ የመናገር ችሎታ የለኝም፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ።” ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍን የፈጠረለት ማነው? ድዳ ወይም ደንቆሮ፥ ዐይኑ እንዲያይ ወይም እንዳያይ የሚያደርግስ ማነው? ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ስለዚህ አሁን ሂድ! እኔም ከአንተ ጋር ሆኜ መናገር እንድትችል አደርጋለሁ፤ ምን መናገር እንደሚገባህ እነግርሃለሁ።” ሙሴም “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለው፤ “ሌዋዊ የሆነው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ ተናጋሪ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልብ ደስ ይለዋል። ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገረውንም ቃል ታስረዳዋለህ፤ ሁለታችሁም እንዴት መናገር እንደምትችሉና ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ አስተምራችኋለሁ፤ እርሱ አንተን ወክሎ ይናገራል፤ በአንተም ስም ቃሉን ለሕዝቡ ያስተላልፋል፤ አንተም ለእርሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ። ተአምራት የምታሳይበትንም ይህን በትር ይዘህ ሂድ።” ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ የትሮ ተመልሶ ሄደና “በግብጽ ወደሚኖሩት ወገኖቼ ተመልሼ ሄጄ በሕይወት መኖራቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። የትሮም ፈቅዶ “በሰላም ሂድ” አለው። ሙሴ ገና በምድያም ሳለ እግዚአብሔር “ሊገድሉህ የሚፈልጉት ሁሉ ስለ ሞቱ ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ” አለው። ስለዚህም ሙሴ ሚስቱንና ወንዶች ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብጽ መጓዝ ጀመረ፤ ተአምራት የሚገለጥበት የእግዚአብሔርንም በትር በእጁ ይዞ ነበር። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ግብጽ መመለስህ ስለ ሆነ፥ በሰጠሁህ ኀይል የምታደርጋቸውን ተአምራት በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ፤ ሆኖም እኔ የፈርዖንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን በቀላሉ አይለቅም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለፈርዖን የምለውን እንዲህ ብለህ ትነግረዋለህ፤ ‘እስራኤል የበኲር ልጄ ነው፤ እኔም ይህ ልጄ እኔን ያመልክ ዘንድ እንድትለቀው ነገርኩህ፤ አንተ ግን እምቢ አልክ፤ ስለዚህ አሁን የአንተን የበኲር ልጅ እገድላለሁ።’ ” ሙሴ ወደ ግብጽ በመጓዝ ላይ ሳለ ባረፈበት ሰፈር እግዚአብሔር አግኝቶት በሞት ሊቀጣው ፈለገ። ከዚያ በኋላ ሲፖራ ሮጣ ሄዳ ባልጩት አመጣችና የልጅዋን ሸለፈት ገረዘች፤ የሙሴንም እግር በሸለፈቱ ዳስሳ “በእርግጥ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። እግዚአብሔርም ለሙሴ ምሕረት አደረገለት፤ እርስዋም “ከግዝረት ሥርዓት የተነሣ አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። በዚያኑ ጊዜ እግዚአብሔር አሮንን “ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ በረሓው ሂድ” አለው። እርሱም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ሄደ፤ በዚያም ሙሴን አግኝቶ ሳመው። ሙሴም እግዚአብሔር ወደ ግብጽ እንዲመለስ ባዘዘው ጊዜ የነገረውን ቃልና እንዲፈጽማቸው ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን አስረዳው። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ወርደው የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን ሁሉ ገለጠላቸው፤ ሙሴም ተአምራትን ሁሉ በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ መጥቶ እንደ ጐበኛቸውና የደረሰባቸውንም የግፍ ጭቈና ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱ።
ዘፀአት 4:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም መለሰ፦ “እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም፦ ‘ጌታ ከቶ አልተገለጠልህም’ ይሉኛል” አለ። ጌታም፦ “ይህ በእጅህ ያለው ምንድነው?” አለው። እርሱም፦ “በትር ነው” አለ። እርሱም “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ እርሱም ወደ መሬት ጣለው፥ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዘው በእጁም ውስጥ በትር ሆነ። “ይህም የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ ጌታ እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው ጌታም ደግሞ፦ “እጅህን ወደ ብብትህ አስገባ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አስገባ፤ ባወጣውም ጊዜ፥ እጁ እንደ በረዶ ነጭ እንደሆነ አየ። እርሱም፦ “እጅህን ወደ ብብትህ መልስ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሰው፥ ከብብቱም ባወጣው ጊዜ ተመልሶ ገላውን እንደሚመስል አየ። “እንዲህ ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ቃል ባይሰሙ፥ የኋላኛይቱን ምልክት ቃል ያምናሉ። እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከዓባይ ወንዝ ጥቂት ውኃን ውሰድ፥ በደረቅ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከዓባይ ወንዝ የወሰድከውም ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም ጌታን፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባርያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፌንና ምላሴን ይይዘኛል።” ጌታም እንዲህ አለው፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳ ወይም ደንቆሮ ወይም የሚያይ ወይም ዕውር ያደረገ ማን ነው? እኔ ጌታ አይደለሁምን? ስለዚህ ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ።” እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለ። የጌታም ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር አውቃለሁ፤ እርሱም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ያይሃልም፤ በልቡም ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ ቃሎቹን በአፉ ታስቀምጣለህ፤ እኔም ከአፍህ ጋርና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ ለአንተ ብሎ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም እንደ እግዚአብሔር ትሆንለታለህ። ይህንንም ተአምራት የምታደርግበትን በትር በእጅህ ይዘኸው ትሄዳለህ።” ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ይትሮ ተመለሰ፥ እርሱም፦ “እባክህን በግብጽ ወዳሉ ዘመዶቼ እንድመለስ እስካሁንም በሕይወት እንዳሉ ሄጄ እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። ይትሮም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። ጌታም ሙሴን በምድያን፦ “ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ ነፍስህን የሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብጽም ምድር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብጽ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ ተመልከት በፈርዖንም ፊት ታደርጋቸዋለህ፤ እኔም ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። ፈርዖንንም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።’” እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በማደሪያው ስፍራ ጌታ ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። ፂፖራም ባልጩት ወሰደች፥ የልጇንም ሸለፈት ገረዘች፥ እግሩንም ነክታ፦ “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ፦ “ለግርዛቱ የደም ሙሽራ” አለች። ጌታም አሮንን፦ “ሙሴን ለመገናኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም። ሙሴም ለአሮን በእርሱ ዘንድ የላከውን የጌታን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎችንም ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም ጌታ ለሙሴ የተናገረውን ቃላት ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቶቹንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ ጌታ የእስራኤልን ልጆች እንደተመለከተ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ ሰገዱም።