ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው። እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው። እግዚአብሔርም፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው። ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች። እግዚአብሔርም “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው። እግዚአብሔርም ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። “አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች። እግዚአብሔርም፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ። እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ጌታ ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋራ ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል። ለርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ ረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል። ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።” ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብጽ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው። ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብጽ ሂድ” አለው። ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብጽ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርም በትር በእጁ ይዞ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብጽ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ” ሙሴ በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። ስለዚህም እግዚአብሔር ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። ሙሴም እግዚአብሔር እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኛቸውና መከራቸውን እንዳየ በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።
ዘፀአት 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 4:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች