ትንቢተ ዳንኤል 6:6-23

ትንቢተ ዳንኤል 6:6-23 አማ05

ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹና ባለሥልጣኖቹ በማደም ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ! አንተ ለዘለዓለም ኑር! እኛ በመንግሥትህ አስተዳደር ሥራ ላይ የተመደብን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ ዐቃብያነ ሕግ፥ እንደራሴዎች፥ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎች የተስማማንበት አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ከአሁን ጀምሮ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው ጸሎት እንዳይደረግ ዐዋጅ እንድታስነግር ነው፤ ይህንንም ዐዋጅ የሚተላለፍ ቢኖር በአንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል እዘዝ። እንግዲህ ንጉሥ ሆይ! ይህ ዐዋጅ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ እንዲሆን ፈርምበት።” በዚህም ዐይነት ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁን በፊርማ አጸና። ዳንኤል ዐዋጁ ተፈርሞበት እንደ ጸና ቢያውቅም እንኳ ወደሚኖርበት ሰገነት ወጣ፤ የሚኖርበትም ሰገነት በኢየሩሳሌም ትይዩ የተከፈቱ መስኮቶች ነበሩት፤ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደ ነበረም በጒልበቱ በመንበርከክ አምላኩን እያመሰገነ በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ ነበር። እነዚህም ዐድመኞች በአንድነት ሄደው፥ ዳንኤል ወደ ፈጣሪው ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ሁሉም በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው የወጣውን ዐዋጅ በመጣሱ ዳንኤልን እንዲህ ብለው ከሰሱት፦ “ንጉሥ ሆይ፥ እስከ ሠላሳ ቀን ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው የሚጸልይ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ ፈርመህበት አልነበረምን?” ንጉሡም “አዎ፥ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ ዐዋጅ ወጥቶአል” አለ። እነርሱም “እንግዲያውስ ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልንም ለማዳን ወሰነ፤ ፀሐይም እስክትጠልቅ ድረስ እርሱን ለማዳን የሚችልበትን ዘዴ ሁሉ ለማግኘት ሞከረ። ሰዎቹም በአንድነት ወደ ንጉሡ መጥተው “ንጉሥ ሆይ! በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት አንድ ንጉሥ ያስተላለፈው ዐዋጅ ወይም ትእዛዝ መለወጥ እንደማይችል ዕወቅ!” አሉት። ስለዚህ ዳንኤል ተይዞ መጥቶ ወደ አንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል ንጉሡ አዘዘ፤ ዳንኤልንም “ሁልጊዜ በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ያድንህ” አለው። በጒድጓዱም አፍ ላይ ድንጋይ ተገጠመበት፤ ማንም ሰው ዳንኤልን አውጥቶ ለማዳን እንዳይሞክር ንጉሡ የራሱን መንግሥታዊ ማኅተምና የባለሟሎቹን ማኅተም አተመበት። ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ ምግብ አልበላም፤ የሚያስደስት ነገርም እንዲቀርብለት ሳይፈልግ እንቅልፍ አጥቶ ዐደረ። በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ ንጉሡ ተነሥቶ በፍጥነት ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ ሄደ። እዚያም በደረሰ ጊዜ ሐዘን በተሞላበት ድምፅ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ! ዘወትር በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ። ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! አንበሶቹ እንዳይጐዱኝ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አፋቸውን ዘጋ፤ ይህንንም ያደረገው እኔ በእርሱ ዘንድ ንጹሕ መሆኔንና አንተንም አለመበደሌን ስላወቀ ነው።” ንጉሡም እጅግ ደስ አለው፤ ዳንኤልንም ከጒድጓዱ ውስጥ እንዲያወጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ባወጡትም ጊዜ በእግዚአብሔር በመታመኑ በሰውነቱ ላይ ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ታወቀ።