የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 6:6-23

ዳንኤል 6:6-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ ሰውም ሆነ ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ፣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፣ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጕድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል። ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።” ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ። ዳንኤልም ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ። ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው፣ ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማጸን አገኙት። ወደ ንጉሡም ሄደው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ፣ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት። ንጉሡም፣ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተንም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ዐዘነ፤ ዳንኤልን ለማዳን ወሰነ፤ ፀሓይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ ያወጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት። ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶችም ጕድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ያድንህ” አለው። ድንጋይ አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም፣ በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማኅተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች ዐተመበት። ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ። በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፤ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጕድጓድ እየተጣደፈ ሄደ። ወደ ጕድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሏልን?” ብሎ ተጣራ። ዳንኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለ ተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ፣ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጐዱኝም።” ንጉሡ እጅግ ተደስቶ፤ ዳንኤልን ከጕድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ነበርና ከጕድጓድ በወጣ ጊዜ፣ አንዳች ጕዳት አልተገኘበትም።

ዳንኤል 6:6-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ። አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ። ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ። ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፥ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፥ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም። እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ፦ ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው። የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት። ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፥ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ። የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፥ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው። ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፥ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው። ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ ሳይበላም አደረ፥ መብልም አላመጡለትም፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ። ወደ ጉድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፥ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው። ዳንኤልም ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው። የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፥ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።

ዳንኤል 6:6-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹና ባለሥልጣኖቹ በማደም ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ! አንተ ለዘለዓለም ኑር! እኛ በመንግሥትህ አስተዳደር ሥራ ላይ የተመደብን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ ዐቃብያነ ሕግ፥ እንደራሴዎች፥ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎች የተስማማንበት አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ከአሁን ጀምሮ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው ጸሎት እንዳይደረግ ዐዋጅ እንድታስነግር ነው፤ ይህንንም ዐዋጅ የሚተላለፍ ቢኖር በአንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል እዘዝ። እንግዲህ ንጉሥ ሆይ! ይህ ዐዋጅ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ እንዲሆን ፈርምበት።” በዚህም ዐይነት ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁን በፊርማ አጸና። ዳንኤል ዐዋጁ ተፈርሞበት እንደ ጸና ቢያውቅም እንኳ ወደሚኖርበት ሰገነት ወጣ፤ የሚኖርበትም ሰገነት በኢየሩሳሌም ትይዩ የተከፈቱ መስኮቶች ነበሩት፤ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደ ነበረም በጒልበቱ በመንበርከክ አምላኩን እያመሰገነ በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ ነበር። እነዚህም ዐድመኞች በአንድነት ሄደው፥ ዳንኤል ወደ ፈጣሪው ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ሁሉም በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው የወጣውን ዐዋጅ በመጣሱ ዳንኤልን እንዲህ ብለው ከሰሱት፦ “ንጉሥ ሆይ፥ እስከ ሠላሳ ቀን ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው የሚጸልይ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ ፈርመህበት አልነበረምን?” ንጉሡም “አዎ፥ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ ዐዋጅ ወጥቶአል” አለ። እነርሱም “እንግዲያውስ ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልንም ለማዳን ወሰነ፤ ፀሐይም እስክትጠልቅ ድረስ እርሱን ለማዳን የሚችልበትን ዘዴ ሁሉ ለማግኘት ሞከረ። ሰዎቹም በአንድነት ወደ ንጉሡ መጥተው “ንጉሥ ሆይ! በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት አንድ ንጉሥ ያስተላለፈው ዐዋጅ ወይም ትእዛዝ መለወጥ እንደማይችል ዕወቅ!” አሉት። ስለዚህ ዳንኤል ተይዞ መጥቶ ወደ አንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል ንጉሡ አዘዘ፤ ዳንኤልንም “ሁልጊዜ በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ያድንህ” አለው። በጒድጓዱም አፍ ላይ ድንጋይ ተገጠመበት፤ ማንም ሰው ዳንኤልን አውጥቶ ለማዳን እንዳይሞክር ንጉሡ የራሱን መንግሥታዊ ማኅተምና የባለሟሎቹን ማኅተም አተመበት። ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ ምግብ አልበላም፤ የሚያስደስት ነገርም እንዲቀርብለት ሳይፈልግ እንቅልፍ አጥቶ ዐደረ። በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ ንጉሡ ተነሥቶ በፍጥነት ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ ሄደ። እዚያም በደረሰ ጊዜ ሐዘን በተሞላበት ድምፅ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ! ዘወትር በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ። ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! አንበሶቹ እንዳይጐዱኝ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አፋቸውን ዘጋ፤ ይህንንም ያደረገው እኔ በእርሱ ዘንድ ንጹሕ መሆኔንና አንተንም አለመበደሌን ስላወቀ ነው።” ንጉሡም እጅግ ደስ አለው፤ ዳንኤልንም ከጒድጓዱ ውስጥ እንዲያወጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ባወጡትም ጊዜ በእግዚአብሔር በመታመኑ በሰውነቱ ላይ ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ታወቀ።