ትንቢተ ዳንኤል 6
6
ዳንኤል በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደ ተጣለ
1ዳርዮስ በመንግሥቱ ግዛት ሁሉ ላይ እንዲያስተዳድሩ መቶ ኻያ አገረ ገዢዎች ለመሾም ፈለገ። 2በተጨማሪም የንጉሡ ቅርብ ረዳቶች ሆነው ንጉሡ ምንም ነገር እንዳይጐድልበት አገረ ገዢዎቹን እንዲቈጣጠሩ ዳንኤልንና ሌሎችን ሁለት ሰዎች መረጠ። 3ዳንኤል ባለው ልዩ የሥራ ችሎታ ከሌሎቹ አገረ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች በልጦ መገኘቱን በተግባር አስመሰከረ፤ ስለዚህ ንጉሡ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሊሾመው አሰበ። 4ከዚህ በኋላ ሌሎቹ አገረ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች በዳንኤልና በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ወንጀል ለማግኘት ፈለጉ፤ ነገር ግን ዳንኤል እጅግ ጠንቃቃና ታማኝ ስለ ነበር ምንም ዐይነት ስሕተት ወይም በደል ሊያገኙበት አልቻሉም። 5ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ከአምላኩ ሕግ በቀር ዳንኤልን የምንከስበት ምንም ዐይነት በደል ማግኘት አልቻልንም” ተባባሉ።
6ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹና ባለሥልጣኖቹ በማደም ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ! አንተ ለዘለዓለም ኑር! 7እኛ በመንግሥትህ አስተዳደር ሥራ ላይ የተመደብን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ ዐቃብያነ ሕግ፥ እንደራሴዎች፥ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎች የተስማማንበት አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ከአሁን ጀምሮ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው ጸሎት እንዳይደረግ ዐዋጅ እንድታስነግር ነው፤ ይህንንም ዐዋጅ የሚተላለፍ ቢኖር በአንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል እዘዝ። 8እንግዲህ ንጉሥ ሆይ! ይህ ዐዋጅ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ እንዲሆን ፈርምበት።” 9በዚህም ዐይነት ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁን በፊርማ አጸና። 10ዳንኤል ዐዋጁ ተፈርሞበት እንደ ጸና ቢያውቅም እንኳ ወደሚኖርበት ሰገነት ወጣ፤ የሚኖርበትም ሰገነት በኢየሩሳሌም ትይዩ የተከፈቱ መስኮቶች ነበሩት፤ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደ ነበረም በጒልበቱ በመንበርከክ አምላኩን እያመሰገነ በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ ነበር።
11እነዚህም ዐድመኞች በአንድነት ሄደው፥ ዳንኤል ወደ ፈጣሪው ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። 12ሁሉም በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው የወጣውን ዐዋጅ በመጣሱ ዳንኤልን እንዲህ ብለው ከሰሱት፦ “ንጉሥ ሆይ፥ እስከ ሠላሳ ቀን ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው የሚጸልይ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ ፈርመህበት አልነበረምን?”
ንጉሡም “አዎ፥ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ ዐዋጅ ወጥቶአል” አለ።
13እነርሱም “እንግዲያውስ ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።
14ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልንም ለማዳን ወሰነ፤ ፀሐይም እስክትጠልቅ ድረስ እርሱን ለማዳን የሚችልበትን ዘዴ ሁሉ ለማግኘት ሞከረ።
15ሰዎቹም በአንድነት ወደ ንጉሡ መጥተው “ንጉሥ ሆይ! በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት አንድ ንጉሥ ያስተላለፈው ዐዋጅ ወይም ትእዛዝ መለወጥ እንደማይችል ዕወቅ!” አሉት።
16ስለዚህ ዳንኤል ተይዞ መጥቶ ወደ አንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል ንጉሡ አዘዘ፤ ዳንኤልንም “ሁልጊዜ በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ያድንህ” አለው። 17በጒድጓዱም አፍ ላይ ድንጋይ ተገጠመበት፤ ማንም ሰው ዳንኤልን አውጥቶ ለማዳን እንዳይሞክር ንጉሡ የራሱን መንግሥታዊ ማኅተምና የባለሟሎቹን ማኅተም አተመበት። 18ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ ምግብ አልበላም፤ የሚያስደስት ነገርም እንዲቀርብለት ሳይፈልግ እንቅልፍ አጥቶ ዐደረ።
19በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ ንጉሡ ተነሥቶ በፍጥነት ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ ሄደ። 20እዚያም በደረሰ ጊዜ ሐዘን በተሞላበት ድምፅ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ! ዘወትር በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ።
21ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! 22አንበሶቹ እንዳይጐዱኝ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አፋቸውን ዘጋ፤ ይህንንም ያደረገው እኔ በእርሱ ዘንድ ንጹሕ መሆኔንና አንተንም አለመበደሌን ስላወቀ ነው።”
23ንጉሡም እጅግ ደስ አለው፤ ዳንኤልንም ከጒድጓዱ ውስጥ እንዲያወጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ባወጡትም ጊዜ በእግዚአብሔር በመታመኑ በሰውነቱ ላይ ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ታወቀ። 24ከዚህም በኋላ ዳንኤልን የከሰሱት ሰዎች ተይዘው እንዲመጡ ንጉሡ አዘዘ፤ እነርሱም ተይዘው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንዲጣሉ አደረገ፤ ገና ወደ ጒድጓዱ አዘቅት ሳይደርሱም አንበሶቹ ቦጫጨቋቸው፤ አጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።
25ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ በየአገሩ ለሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ነገዶች በጽሑፍ እንዲህ የሚል መልእክት አስተላለፈ፥
“ሰላም ለእናንተ ይሁን! 26በመንግሥቴ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር በዐዋጅ አዝዤአለሁ፤
“እርሱ ሕያውና ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፤
መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፤
ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤
27እርሱ ያድናል ይታደግማል፤
እርሱ በሰማይና በምድር ድንቅ ነገሮችንና ተአምራትን ያደርጋል፤
እርሱ ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ አድኖአል።”
28ዳንኤልም በዳርዮስና በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት ሁሉ እንደ ተከበረ ኖረ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997