የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ። አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ። ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ። ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፥ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፥ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም። እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ፦ ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው። የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት። ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፥ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ። የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፥ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው። ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፥ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው። ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ ሳይበላም አደረ፥ መብልም አላመጡለትም፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ። ወደ ጉድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፥ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው። ዳንኤልም ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው። የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፥ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።
ትንቢተ ዳንኤል 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 6:6-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች