ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-14

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-14 አማ05

አሳ በይሁዳ ላይ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፥ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ይሁዳን ወረረ፤ ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባ፥ ከይሁዳም ማንም እንዳይወጣ ለማድረግ ራማን መመሸግ ጀመረ፤ ስለዚህም አሳ ከቤተ መቅደስና ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ብርና ወርቅ በማውጣት በደማስቆ ይኖር ለነበረው ለሶርያው ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ “የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዐይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላኩልህ ገጸ በረከት ነው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።” ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበለት ሐሳብ በመስማማት የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን ልኮ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ ሠራዊቱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካ ተብለው የሚጠሩትን ከተሞችና በንፍታሌም ግዛት ስንቅና ትጥቅ የሚቀመጥባቸውን ከተሞች ሁሉ በድል አድራጊነት ያዙ፤ ንጉሥ ባዕሻ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን ለመመሸግ የጀመረውን ሥራ ተወ፤ ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሳ ሰዎችን ከመላ ይሁዳ ሰብስቦ ንጉሥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ ይጠቀምበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ከዚያ ወስደው የጌባዕንና የምጽጳን ከተማዎች መሸጉባቸው። በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐናኒ ወደ ንጉሥ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በእግዚአብሔር በመተማመን ፈንታ በሶርያ ንጉሥ ስለ ተማመንክ የእስራኤል ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል፤ ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠራዊት፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞች አልነበሩአቸውምን? ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ አንተ በእግዚአብሔር ስለ ታመንክ፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደረገህ። እግዚአብሔር መላውን ዓለም አተኲሮ በመመልከት፥ በሙሉ ልባቸው በእርሱ ለሚተማመኑት ሁሉ ብርታትን ይሰጣቸዋል፤ እንግዲህ አንተ የሞኝነት ሥራ ስለ ፈጸምክ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይለይህም፤” ይህ አነጋገር አሳን እጅግ ስላስቈጣው ነቢዩን በብረት ሰንሰለት አስሮ ወህኒ አስገባው፤ ከዚህም ጊዜ አንሥቶ፥ ንጉሥ አሳ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹን በጭካኔ ማንገላታት ጀመረ። በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተፈጸሙ ድርጊቶች ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ፤ አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሩን በጠና ታመመ ይህም ሆኖ ሳለ እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም፤ አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ሬሳውም በልዩ ቅመማ ቅመምና በሽቶ ታሽቶ እርሱ ራሱ በዳዊት ከተማ ከአለት አስፈልፍሎ ባሠራው መቃብር ተቀበረ፤ ስለ ክብሩም ብዙ እንጨት ከምረው በማንደድ ታላቅ ለቅሶ አደረጉለት።