አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት። አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሃዳድ ላከ፤ “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረ ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑር። እነሆ፤ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ። ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋራ ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው። ቤን ሃዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ። እነርሱም ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤል ማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ግምጃ ቤት ከተሞችን ሁሉ ድል አድርገው ያዙ። ባኦስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ። ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም ባኦስ በራማ ሲሠራበት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት ወሰዱ፤ አሳም ጌባዕንና ምጽጳን ሠራበት። በዚያ ጊዜም ባለራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ሳይሆን በሶርያ ንጉሥ ስለ ታመንህ፣ የሶርያ ንጉሥ ሰራዊት ከእጅህ አምልጧል። ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ቍጥር ካላቸው ሠረገላዎቻቸውና ፈረሶቻቸው ጋራ ኀያል ሰራዊት አልነበሩምን? ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጠህ፤ በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራህ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።” ከዚህ የተነሣም አሳ ባለራእዩን ተቈጣው፤ በጣም ስለ ተናደደም እስር ቤት አስገባው። በዚያ ጊዜም አሳ አንዳንድ ሰዎችን ክፉኛ አስጨነቃቸው። በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ሥራ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተጽፏል። አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሮቹን ታመመ፤ ሕመሙ ቢጸናበትም እንኳ፣ በዚያ ሁሉ ሕመም የባለመድኀኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም። አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ፤ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ። በዳዊት ከተማ ከዐለት አስፈልፍሎ ለራሱ ባሠራውም መቃብር ቀበሩት። በቅመማ ቅመምና በልዩ ልዩ ጣፋጭ ሽቱዎች በተሞላ ቃሬዛ ላይ አኖሩት፤ ስለ ክብሩም ትልቅ እሳት አነደዱ።
2 ዜና መዋዕል 16 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 16:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች