የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ዜና መዋዕል 16

16
የአሳ የመጨረሻ ዓመታት
16፥1-6 ተጓ ምብ – 1ነገ 15፥17-22
16፥11–17፥1 ተጓ ምብ – 1ነገ 15፥23-24
1አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ፣ ወደዚያም ማንም እንዳይገባ ለመከልከል ራማን መሸገ።
2አሳም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር ላከ፤ 3ከዚያም “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑረን፤ እነሆ፤ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከባኦስ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው።
4ወልደአዴር የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀበለ፤ የጦር አዛዦቹንም በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ። እነርሱ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልማ ይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ግምጃ ቤት ከተሞች ሁሉ ድል አድርገው ያዙ። 5ባኦስ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ። 6ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት ወሰዱ፤ አሳም ጌባንና ምጽጳን ሠራባት።
7በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ሳይሆን በሶርያ ንጉሥ ስለ ታመንህ፣ የሶርያ ንጉሥ ሰራዊት ከእጅህ አምልጧል። 8ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ቍጥር ካላቸው ሠረገላዎቻቸውና#16፥8 ወይም ሠረገለኞች ፈረሶቻቸው ጋር ኀያል ሰራዊት አልነበሩምን? ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጠህ፤ 9በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራህ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።”
10ከዚህ የተነሣም አሳ ባለ ራእዩን ተቈጣው፤ በጣም ስለ ተናደደም እስር ቤት አስገባው። በዚያን ጊዜም አሳ አንዳንድ ሰዎችን ክፉኛ አስጨነቃቸው።
11በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ሥራ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መዛግብት ተጽፏል። 12አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሮቹን ክፉኛ ታመመ፤ ሕመሙ ቢጸናበትም እንኳ፣ በዚያ ሁሉ ሕመም የባለ መድኀኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም። 13አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ፤ እንደ አባቶቹም ሁሉ አንቀላፋ። 14በዳዊት ከተማ ከዐለት አስፈልፍሎ ለራሱ ባሠራውም መቃብር ቀበሩት። በቅመማ ቅመምና በልዩ ልዩ ጣፋጭ ሽቱዎች በተሞላ ቃሬዛ ላይ አኖሩት፤ ስለ ክብሩም ትልቅ እሳት አነደዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ