2 ዜና መዋዕል 16:1-14
2 ዜና መዋዕል 16:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራት። አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሥ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ፦ በደማስቆ ወደ ተቀመጠው ወደ ሶርያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር ላከ። እንዲህም አለው፦ “በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል አድርግ፤ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ መጥተህ ትወጋው ዘንድ እነሆ፥ ወርቅና ብር ልኬልሃለሁ።” ወልደ አዴርም ንጉሡን አሳን ሰማው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰደደ፤ እነርሱም አእዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና የንፍታሌምንም አውራጃ ከተሞች ሁሉ መቱ። ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፤ ሥራውንም አቋረጠ። የይሁዳ ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰደ፤ እርሱም ገባዖንንና መሴፋን ሠራበት። በዚያን ጊዜም ነቢዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፥ “በሶርያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጆችህ አምልጠዋል። ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው። እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዐይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ባለማወቅህ በድለሃል፤ ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ጦርነት ይሆንብሃል።” አሳም በነቢዩ በአናኒ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በግዞት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አስጨነቀ። የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። አሳም በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በሕማሙ ጊዜ ባለ መድኀኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላ አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የቀብር ሥርዐት አደረጉለት።
2 ዜና መዋዕል 16:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት። አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሃዳድ ላከ፤ “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረ ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑር። እነሆ፤ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ። ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋራ ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው። ቤን ሃዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ። እነርሱም ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤል ማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ግምጃ ቤት ከተሞችን ሁሉ ድል አድርገው ያዙ። ባኦስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ። ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም ባኦስ በራማ ሲሠራበት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት ወሰዱ፤ አሳም ጌባዕንና ምጽጳን ሠራበት። በዚያ ጊዜም ባለራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ሳይሆን በሶርያ ንጉሥ ስለ ታመንህ፣ የሶርያ ንጉሥ ሰራዊት ከእጅህ አምልጧል። ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ቍጥር ካላቸው ሠረገላዎቻቸውና ፈረሶቻቸው ጋራ ኀያል ሰራዊት አልነበሩምን? ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጠህ፤ በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራህ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።” ከዚህ የተነሣም አሳ ባለራእዩን ተቈጣው፤ በጣም ስለ ተናደደም እስር ቤት አስገባው። በዚያ ጊዜም አሳ አንዳንድ ሰዎችን ክፉኛ አስጨነቃቸው። በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ሥራ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተጽፏል። አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሮቹን ታመመ፤ ሕመሙ ቢጸናበትም እንኳ፣ በዚያ ሁሉ ሕመም የባለመድኀኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም። አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ፤ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ። በዳዊት ከተማ ከዐለት አስፈልፍሎ ለራሱ ባሠራውም መቃብር ቀበሩት። በቅመማ ቅመምና በልዩ ልዩ ጣፋጭ ሽቱዎች በተሞላ ቃሬዛ ላይ አኖሩት፤ ስለ ክብሩም ትልቅ እሳት አነደዱ።
2 ዜና መዋዕል 16:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ “በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሆናል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ” ብሎ በደማስቆ ወደተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ቤንሀዳድ ሰደደ። ቤንሀዳድ ንጉሡን አሳን“እሺ” አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰደደ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ መቱ። ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፤ ሥራውንም አቍረጠ። ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት አስወገዱ፤ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው“በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጅህ አምልጦአል። ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው። እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል።” አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በግዞት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አስጨነቀ። የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላው አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።
2 ዜና መዋዕል 16:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሳ በይሁዳ ላይ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፥ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ይሁዳን ወረረ፤ ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባ፥ ከይሁዳም ማንም እንዳይወጣ ለማድረግ ራማን መመሸግ ጀመረ፤ ስለዚህም አሳ ከቤተ መቅደስና ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ብርና ወርቅ በማውጣት በደማስቆ ይኖር ለነበረው ለሶርያው ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ “የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዐይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላኩልህ ገጸ በረከት ነው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።” ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበለት ሐሳብ በመስማማት የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን ልኮ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ ሠራዊቱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካ ተብለው የሚጠሩትን ከተሞችና በንፍታሌም ግዛት ስንቅና ትጥቅ የሚቀመጥባቸውን ከተሞች ሁሉ በድል አድራጊነት ያዙ፤ ንጉሥ ባዕሻ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን ለመመሸግ የጀመረውን ሥራ ተወ፤ ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሳ ሰዎችን ከመላ ይሁዳ ሰብስቦ ንጉሥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ ይጠቀምበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ከዚያ ወስደው የጌባዕንና የምጽጳን ከተማዎች መሸጉባቸው። በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐናኒ ወደ ንጉሥ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በእግዚአብሔር በመተማመን ፈንታ በሶርያ ንጉሥ ስለ ተማመንክ የእስራኤል ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል፤ ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠራዊት፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞች አልነበሩአቸውምን? ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ አንተ በእግዚአብሔር ስለ ታመንክ፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደረገህ። እግዚአብሔር መላውን ዓለም አተኲሮ በመመልከት፥ በሙሉ ልባቸው በእርሱ ለሚተማመኑት ሁሉ ብርታትን ይሰጣቸዋል፤ እንግዲህ አንተ የሞኝነት ሥራ ስለ ፈጸምክ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይለይህም፤” ይህ አነጋገር አሳን እጅግ ስላስቈጣው ነቢዩን በብረት ሰንሰለት አስሮ ወህኒ አስገባው፤ ከዚህም ጊዜ አንሥቶ፥ ንጉሥ አሳ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹን በጭካኔ ማንገላታት ጀመረ። በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተፈጸሙ ድርጊቶች ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ፤ አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሩን በጠና ታመመ ይህም ሆኖ ሳለ እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም፤ አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ሬሳውም በልዩ ቅመማ ቅመምና በሽቶ ታሽቶ እርሱ ራሱ በዳዊት ከተማ ከአለት አስፈልፍሎ ባሠራው መቃብር ተቀበረ፤ ስለ ክብሩም ብዙ እንጨት ከምረው በማንደድ ታላቅ ለቅሶ አደረጉለት።
2 ዜና መዋዕል 16:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። አሳም ከጌታ ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ወደ ተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር እንዲህ ብሎ ላከ፦ “በአባቴና በአባትህ መካከል እንደነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሁን፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ።” ወልደ አዴር ንጉሡን አሳን እሺ አለው፥ የሠራዊቱንም የጦር አዛዦች በእስራኤል ከተሞች ላይ ላከ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና ለንፍታሌም እንደ ግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ያዙ። ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፥ ሥራውንም አቋረጠ። ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ ዓናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በጌታ አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል። ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ሠራዊት አልነበሩምን? በጌታ ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጌታ ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ለማጽናት ዐይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። እንግዲህ አሁን የሞኞችን ተግባር ፈጽመሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ጦርነት ይደረግብሃል።” አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በቊራኛ አስሮ በወህኒ ቤት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ፥ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አሠቃየ። የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ ጌታን አልፈለገም። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቶ በተሞላው አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።