ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16
16
በይሁዳና በእስራኤል መካከል የተደረገ ጦርነት
(1ነገ. 15፥17-22)
1አሳ በይሁዳ ላይ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት፥ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ይሁዳን ወረረ፤ ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባ፥ ከይሁዳም ማንም እንዳይወጣ ለማድረግ ራማን መመሸግ ጀመረ፤ 2ስለዚህም አሳ ከቤተ መቅደስና ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ብርና ወርቅ በማውጣት በደማስቆ ይኖር ለነበረው ለሶርያው ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ 3“የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዐይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላኩልህ ገጸ በረከት ነው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።”
4ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበለት ሐሳብ በመስማማት የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን ልኮ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ ሠራዊቱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካ ተብለው የሚጠሩትን ከተሞችና በንፍታሌም ግዛት ስንቅና ትጥቅ የሚቀመጥባቸውን ከተሞች ሁሉ በድል አድራጊነት ያዙ፤ 5ንጉሥ ባዕሻ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን ለመመሸግ የጀመረውን ሥራ ተወ፤ 6ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሳ ሰዎችን ከመላ ይሁዳ ሰብስቦ ንጉሥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ ይጠቀምበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ከዚያ ወስደው የጌባዕንና የምጽጳን ከተማዎች መሸጉባቸው።
ነቢዩ ሐናኒ
7በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐናኒ ወደ ንጉሥ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በእግዚአብሔር በመተማመን ፈንታ በሶርያ ንጉሥ ስለ ተማመንክ የእስራኤል ሠራዊት ከእጅህ አምልጦአል፤ 8ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠራዊት፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞች አልነበሩአቸውምን? ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ አንተ በእግዚአብሔር ስለ ታመንክ፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደረገህ። 9እግዚአብሔር መላውን ዓለም አተኲሮ በመመልከት፥ በሙሉ ልባቸው በእርሱ ለሚተማመኑት ሁሉ ብርታትን ይሰጣቸዋል፤ እንግዲህ አንተ የሞኝነት ሥራ ስለ ፈጸምክ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይለይህም፤” 10ይህ አነጋገር አሳን እጅግ ስላስቈጣው ነቢዩን በብረት ሰንሰለት አስሮ ወህኒ አስገባው፤ ከዚህም ጊዜ አንሥቶ፥ ንጉሥ አሳ ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹን በጭካኔ ማንገላታት ጀመረ።
የአሳ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(1ነገ. 15፥23-24)
11በአሳ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተፈጸሙ ድርጊቶች ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ፤ #16፥11 የእስራኤል፦ ወይም የሶርያ። 12አሳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት እግሩን በጠና ታመመ ይህም ሆኖ ሳለ እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የእግዚአብሔርን ርዳታ አልፈለገም፤ 13አሳም በነገሠ በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። 14ሬሳውም በልዩ ቅመማ ቅመምና በሽቶ ታሽቶ እርሱ ራሱ በዳዊት ከተማ ከአለት አስፈልፍሎ ባሠራው መቃብር ተቀበረ፤ ስለ ክብሩም ብዙ እንጨት ከምረው በማንደድ ታላቅ ለቅሶ አደረጉለት።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997